ለሰላም እኩል ዋጋ ከፍለን የሚገኘውን ትርፍ እኩል እንካፈል-ረ/ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ

176
ነሐሴ 9/2011 ለሰላም እኩል ዋጋ ከፍለን የሚገኘውን ትርፍ እኩል መካፈል መቻል ይጠበቅብናል ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ተናገሩ። ከኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ በርካታ ወጣቶች ስለ አንድነትና ሰላም በተዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ በመምከር ላይ ናቸው። ኮንፍረንሱ በሰላም ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጵያውያን የሰላም እሴቶችንና አንድነትን ለማጠናከር ከመግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ ነው። በመድረኩም ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙ ሲሆን "የዛሬዋን ኢትዮጵያን ለማሳደግ ሌላ ትውልድ፣ ሌላ አጋጣሚና ሌላ ጊዜ መጠበቅ አይጠይቅም " ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ ሰላምና አንድነትን ማረጋገጥ መሆኑን አውስተው ያንን ለማረጋገጥ ከአሁኑ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዚህም ቀደም ብለው የነበሩ የመከባበር፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብና አብሮ የመኖር የሰላም እሴቶችን ከማስጠበቅ አልፎ ማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል። የሰላም እሴቶቹ እንዲጎለብቱም እኩል ዋጋ ከፍለን ከሰላም የሚገኘውን ትርፍ እኩል ለመካፈል መነሳት ይኖርብናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ። የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሰላም ባለቤት እንድትሆን ወጣቱ "ባለ ዕዳም ባለ አደራም" ነው ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ ሰላም ለማምጣትም ይሁን ሰላም እንዲጠፋ ትልቅ አቅም እንዳለው ተገንዝቦ አቅሙን ለሰላም ግንባታና ለአገር አንድነት ማዋል ይጠበቅበታል ብለዋል። በተለይም በተለያዩ የፖለቲካ ነጋዴዎች በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎችን ወጣቱ በጥንቃቄ አይቷቸው በምክንያት ሊገነዘባቸው እንደሚገባም እንዲሁ። ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ዜጎችም ምክንያታዊ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል ወይዘሮ አልማዝ። ከተሳታፊ ወጣቶች አንዷ ወጣት መስከረም ተክለ ሃይማኖት በበኩሏ ሰላምንና አንድነትን ለማረጋገጥ ከወጣቱ የሚጠበቁ ነገሮች እንዳሉ ሆነው እንደ ሀገር ገንቢ የሆኑ የመከባበርና የአብሮነት እሴቶች ላይ ተከታታይ የግንዛቤ ስራ መሰራት አለበት ብላለች። ለዚህም ከቤተሰብና ከትምህርት ቤት ጀምሮ የጋራ ታሪኮቻችንን የማስተዋወቅና የስነ ምግባር ትምህርት ማጠናከር ወሳኝ ስራ መሆኑን ተናግራለች። ወጣት ካሳሁን ወርቁ በበኩሉ ሰላም እንዲረጋገጥና አብሮነት እንዲጎለብት ሁላችንም በየአካባቢያችን ለአንድነቱ መስራት አለብን ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም