ትራምፕ በሆንግ ኮንግ ጉዳይ የቻይናውን ፕሬዝዳንት ማነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጹ

88

ኢዜአ ነሃሴ 9/2011 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይናን ፕሬዝዳንት ዚ ጂንፒንግ በሆንግኮንክ የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ በግል ማነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡

ሚስተር ትራምፕ በቲውተር እንደገለፁት የቻይናው ፕሬዝዳንት የሆንግ ኮንግን ጉዳይ” ሰብአዊነት በተሞላበት መንገድ እንደሚፈቱት ጥርጣሬ የለኝም” ብለዋል፡፡

የሆንግኮንግን አመፅ ከአሜሪካና ቻይና የንግድ ድርድር ጋር ያቆራኙት ሚስተር ትራምፕ ሁኔታው የንግድ ውጥረትን ማባባሱን ተናግረዋል፡፡

“ቻይና ድርድሩን ማድረግ ብትሻም ፤ቅድሚያ ግን የሆንግ ኮንግን ጉዳይ በጋራና በሰብአዊነት እንፍታው” ብለዋል ሚስተር ትራምፕ፡፡

ሚስተር ትራምፕ አስተያየቱን የሰጡት ወንጀለኞችን አሳልፎ የሚሰጠውን ህግ በመቃወም ለሳምንት ሲካሄድ ከቆየው አመፅ በኋላ ነው፡፡

ተቺዎች ስጋታቸውን እንዳስቀመጡት ህጉ ሆንግኮንግን ይበልጥ በቻይና ቁጥጥር ስር እንድትውል ያደርጋታል ፡፡

ህጉ ለጊዜው የታገደ ቢሆንም አማፂዎቹ ጥያቄያቸውን ከፍ ወደ አለ የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ  አሳድገውታል፡፡

ሆንግ ኮንግ  “አንድ ሃገር ሁለት አስተዳደር” በሚል ስርአት የቻይና አካል ስትሆን ይህም የራሷን የአስተዳደር ነፃነት ይበልጥ አጎናፅፏታል ነው የተባለው፡፡

የራሷ የህግና የዳኝነት ስርአት ያላት ሆንግኮንግ ከዋናዋ ሀገር ቻይና የማይስተዋሉ ነፃነቶች አሏት ያለው የቢቢሲ ዘገባ ለአብነት የመታሰቢያ በአላትን በቲያናሚን አደባባይ ማሰብን ለአብነት አንስቷል፡፡