ዩኒቨርሲቲዎችን የሰላም አውድማ ለማድረግ የታየው በጎ ጅምር !

83
ሚፍታህ አህመድ/ ከኢዜአ/ ማርቲን ሉተር “ ሰዎች ሊጋጩ ይችላሉ ይልና ለምን ሊጋጩ ይችላሉ ? ብሎ መልሶ እራሱን ይጠይቃል ።  ለራሱ መልስ ሲሰጥ ደግሞ  ስለሚፈራሩ ነው ይላል ፡፡ ለምን ይፈራራሉ ? የሚለውን ደግሞ መልሶ ለራሱ ያቀረበው ጥያቄ ነበር ። ስለማይተዋወቁ ነው የሚል ምላሽ ይሰጣል ። ለምን አይተዋወቁም ? በማለት እንደገና ይጠይቃል ፡፡ ተለያይተው ስለሚኖሩ ነው “ በማለት ሃሳቡን ያሳርጋል ። ከላይ የሰፈረውን የማርቲን ሉተር አባባል ያጋሩን በጅማ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር ልማት ትምህርት ክፍል የስነዜጋ መምህር የሆኑት አቶ አብዮት ደስታ ናቸው ። ሰዎች በመልከዓ  ምድር ብቻ ሳይሆን በሃሳብና በአመለካከት ከተለያዩ አለመተማመን በመካከላቸው ስለሚፈጠር አለመግባባቶች እያደጉ ሂደው ለአገር ጭምር አደጋ ይሆናሉ ባይ ናቸው ፡፡ መፍትሔው  ደግሞ በመቀራረብ አንዱ ስለሌላው ጠንቅቆ እንዲያውቅ ማድረግ ነው የሚል ፅኑ እምነት አላቸው ፡፡ ፌዴራላዊው ስርዓታችን  ደግሞ እርስ በርሳችን ለመተዋወቅ አመቺ እንደሆነ ይናገራሉ ። የጅማ ዩኒቨርሲቲ የነገውን ሀገር የሚረከቡ ወጣት ምሁራን እርስ በርሳቸው እንዲቀራረቡ ፣ በሚገባ እንዲተዋወቁና ጤናማና ሰላማዊ ግንኝነት እንዲያዳብሩ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ። ዩኒቨርስቲው ከሰላም ልማት ማዕከል ጋር በመተባበር ተማሪዎች ብቻ የሚሳተፉበት ተከታታይ የውይይት መድረክ (sustained dialogue)  ፈጥሯል ፡፡ የጅማ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክትሬት ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ በየነ “ በዩኒቨርስቲው የተረጋጋ የመማር ማስተማር፣    የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ የተሳካ ለማድረግ ሰላም የሚያስብ አዕምሮ  በዩኒቨርስታችን ውስጥ ማበብ “ አለበት ይላሉ ፡፡ የሰላም ማዕከሉ በጅማ ዩኒቨርስቲ ዋናው ጊቢ 600 ለሚደርሱ ከተለያዩ እምነት፣ባህልና የትምህርት ክፍል ለተውጣጡ ተማሪዎች ተከታታይነት ያለው የሰላም ውይይት እንዲካሔድ እያደረገ ነው ፡፡ በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ተማሪዎች ደግሞ በፍርሃት ይተያዩ የነበሩ ናቸው ። መድረኩ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ የመጡ ተማሪዎች አንዱ ስለሌላው የተሻለ እውቀትና ግንዛቤ በማግኘት ጤናማ  ግንኙነት መፍጠር እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ አንዱ ሌላውን የማዳመጥ ባህል እንዲያጎለብትና የየማህበረሰባቸውን እሴት ለመለዋወጥ እድል እንዲያገኙ አስችሏቸዋል ይላሉ ፡፡ በቀጣይ ከዋናው ጊቢ ውጭ ወደ ሚገኙት ሁለት ኮሌጆች ለማስፋፋት እንደሚሰሩም ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል ፡፡ በፌደራል አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች የመንግስታት ግንኙነት ማጠናከር ዳይሬክትሬት ጀነራል የፌደራሊዝም አስተምህሮትና ስርፀት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን የኢትዮጵያ የፌደራል ስርአት የብዝሃነትን ጥያቄ በመመለስ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያብራራሉ ፡፡ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቀራርበው በመነጋገር መተዋወቅ እንዲችሉ የጋራ እሴት እንዲገነቡ የፌዴራል ስርአቱ ያግዛቸዋል ፡፡ የሰላም ልማት ማዕከል ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ ንጉሴ አንጌሳ በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርት የሚማሩ ተማሪዎች የተለያየ እምነት፣ባህል፣ አስተሳሰብ ይዘው በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩና የሚማሩ ከመሆናቸው አንጻር መቀራረቡ ለሁሉም የሚበጅ ነው ። ተማሪዎች ለተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ለእምነቶች፣ባህሎችና አስተሳሰቦች የሚኖራቸው ክብር ባላቸው መረጃና ዕወቀት ልክ ነው፡፡ ያላቸው መረጃና ዕውቀት የተዛባ ከሆነ የጋራ አላማ ለማሳካት የሚቸገሩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በአብዛኛው ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በግለሰብ ደረጃ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ቡድን አድገው ለአገር ጭምር ችግር ወደ መሆን የሚቃረቡበት ሁኔታ የሚስተዋለውም ከመረጃ ክፍተት የሚመነጭ ሊሆን ይችላል ። ይህንኑ መሰል  ችግር ለመቅረፍ ደግሞ የሰላም እሴት ግንባታ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ባይ ናቸው ፡፡ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላም እሴት ግንባታ ተጀምሮ ውጤታማ በመሆኑ ምክንያት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ባደረገው ድጋፍ በባርዳር፣ ጎንደር፣ በአምቦ፣ በሃሮማያና በጅማ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ተከታታይ ውይይት ተግባራዊ በመሆን ላይ እንደሚገኝ አቶ ንጉሴ ገልፀዋል ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ 2 ሺ 100 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተከታታይ ውይይቱ ተሳታፊዎች ሆነዋል ። ተማሪዎች ውይይቱን የሚያደረጉት በቡድን ተደራጅተው ሲሆን አንድ ቡድን 12 አባላት አሉት፡፡ በአመት ውስጥ በሚመቻችላቸው ጊዜና ቦታ በሳምንት አንድ ጊዜ ለሁለት ሰአታት በአመት ቢያንስ 14 ጊዜ እየተገናኙ ይወያያሉ ፡፡ ተማሪዎች በሚያደርጉት የውይይት ሂደት ውስጥ የማንንም ባህል፣እምነት ብሄር ወክለው አይደለም፡፡ በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ ምዘናዎችና በፕሮግራሙ ፋይዳ ዙሪያ የተካሔዱ የጥናት ውጤቶች እንዳመላከቱት ውይይቶቹ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ የጎላ ሚና እንዳላቸውና ተማሪዎችም በሰላም፣በፍቅር፣ በመከባበር እንዲኖሩ የሚያስችል መሆኑን ተረጋግጧል ይላሉ ፡፡ ተማሪዎች በአንድ የውይይት አመት ውስጥ የእኔ ሃሳብ ብቻ ይደመጥ፣ የኔ ብቻ ትክክል ነው፣ የእኔ ኃይማኖትና ብሄር ብቻ ትክክል ነው ከማለት ውጥተው አንዱ የሌላን አመለካከት የማክበርና አብሮ በሰላም ለመኖር የሚያስችል ስብዕና እየተላበሱ መምጣታቸውን በጥናቱ ተረጋግጧል ። የሁለተኛ አመት የአካውንቲንግ ተማሪ መቅደስ ዘውዲቱ “ በሰላም ልማት ማዕከል ለአንድ አመት ያደረኩት ውይይት የተለያዩ ባህል ካላቸው ሰዎች ጋር በፍቅር አብሬ እንድኖር የሚስችል አስተሳሳብ እንዲይዝ አግዞኛል” ትላለች ፡፡ ተማሪዎች በጋራ በምናደረገው ውይይት የመደማመጥና የመወያየት ባህል እንድናዳበር ከማድረጉም በላይ ማደግ ባለብን የዕወቅት ደረጃ እንድናድግና እንድንበስል ረድቶናል የሚል አስተሳሰብ አላት ፡፡ ውይይቱ ካለው የላቀ ፋይዳ አንፃር የሚያሳትፋቸው የተማሪዎች ቁጥር ቢጨምርና ወደ ሌሎች ዪኒቨርሲቲዎችም ቢስፋፋ መልካም ነው  የሚል አስተያየትም አላት ።የተማሪ መቅደስ አስተያየት እውነት  ነውና መልካም ጅምሩ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም