ታንዛኒያ 50 ሚሊዮን ችግኞችን በኪሊማንጃሮ ተራራ ላይ የመትከል ዕቅድ አላት

62
ኢዜአ ነሃሴ 8/2011 ታንዛኒያ ‘ትሪስ 4 ኪሊ’ ብላ በሰየመችው ስትራቴጂክ ፕሮጀክቷ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ የዛፍ ችግኝ በኪሊማንጃሮ ተራራ ልትተክል እንደሆነ ማስታወቋን ኦል-አፍሪካ ዶት ኮም ድረ ገፅ አስነበበ፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዳይሬክተር ቶማስ ሙኖ በዚህ የክረምት ወቅት የሚተከሉት ችግኞች ድርቅና በረሃማነትን ለመዋጋት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚከናወንበት ቦታ በአፍሪካ ከፍተኛ ቦታ በሆነው በታዋቂው የኪሊማንጃሮ ተራራ ሲሆን ተራራውን ወደ ነበረበት ገፅታ በመመለስ የአረንጓዴ ውበት እንዲላበስ ያደርገዋል ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ያስታወቁ ሲሆን የሚተከሉ ችግኞችም ለፍሬ እስኪበቁ ድረስ ክትትል አይለያቸውም ብለዋል፡፡ በኪሊ-ማንጃሮ ተራራ አካባቢ ዛፎች መድረቃቸውና አዳዲስ ችግኞች አለመተከላቸው የተራራው ጫፍ በረዶ እየቀለጠ መምጣቱ ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑም ዳይሬክተር ቶማስ ሙኖ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ምክኒያትም በአካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ የዝናብ መቀነስ እየተስተዋለ መምጣቱን በዘገባው ሰፍሯል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለማቃለል እንዲሁም ለከሰል በሚል ሰበብ ዛፍ ማቃጠልንና ዛፎችን ለማገዶ መጠቀም ያሉ ሰዋዊ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር የተቀናጀ ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በርካታ ወጣቶች በዚህ ግብርና እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሚስተር ቶማስ ሞኖ ሲቀጥሉም የትሪ 4 ኪሊ ፕሮጀክት በኪሊ-ማንጃሮ አካባቢ የተጀመረ ሲሆን የአካባቢውን መጎሳቆልን ለመፈተሸ የሚረዳና ሰዎችም ችግኝ እንዲተክሉ ያነሳሳል ብለዋል፡፡ ይህንን የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት በገንዘብ ለመደገፍ የሆሰኑ የዱር እንስሳት ጥበቃና በታንዛኒያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የቢራ አምራች ኩባንያዎች ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ህዝቡ፣ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለሙያዎችና የአከባቢው የመንግስት ባለስልጣናት እጅ ለእጅ ተያይዘው አንድ ላይ እንዲወጡ ዳይሬክተሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኦል-አፍሪካ በማጠቃለያ ዘገባው አስፍሯል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም