ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከሉ ችግኞች እየተንከባከበ ነው

79

አምቦ (ኢዜአ) ነሐሴ 8 / 2ዐ11  በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከሉ ችግኞች ተንከባክበው በማሳደግ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየሰሩ መሆናቸውን በምእራብ ሸዋ ዞን የአምቦና የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ ፡፡

በምእራብ ሸዋ ዞን በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከሉ ከ19 ሚሊየን በላይ  ችግኞች ተንከባክቦ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ተብሏል ።

የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ አቶ አለበል መንግስቱ በሰጡት አስተያየት በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተከሉዋቸውን ችግኞች በእንክብካቤ አሳድገው ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የአረምና የኩትኳቶ ስራዎች በማከናውን ላይ ናቸው ።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ በላቸው ጫላ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተከሉዋቸውን ችግኞች እንዲፀድቁ በመኮትኮትና አፈር በማልበስ ሥራዎች ላይ ጠንክረው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።

ችግኞችን ለማጽደቅ የሚደርጉትን ስራ በበጋ ወራትም እንደሚቀጥሉበት ገልፀዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከሉትን ተንከባክቦ ማሳደግ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነት ነው ያሉት ደግሞ የአምቦ ወረዳ ነዋሪ አቶ ኢዶሳ ያደሳ ናቸው፡፡

ችግኞቹ በተተከሉባቸው ቦታዎች ውሃ እንዳይተኛና አፈሩን እንዳይሸረሽር  እየተንከባከቡ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የምእራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ደበሎ በበኩላቸው በዞኑ 22ቱም ወረዳዎች በክረምት ወራት 154 ሚሊየን የተለያዩ ችግኞችን መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡

ቀጣይነት ላለው ለችግኝ እንክብካቤ ስራው የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እያረጉ እንደሆነም አቶ ከበደ ተናግረዋል፡፡

በልማቱም ከ287 ሺህ በላይ ሕዝብ መሆኑን ከዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።