የአየር ንብረት ለውጥ በዩጋንዳ የወባ ወረርሽኝ እንዲባባስ አድርጓል ተባለ

69
ኢዜአ ነሃሴ 8/2011በዩጋንዳ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የወባ ወረርሽኝ ተጠቂ መሆናቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት ለበሽታው ስርጭት መባባስ ምክንያት እንደሆነ የዩጋንዳ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል። ከዚህ ቀደም ከበሽታ ነፃ የሆኑ አካባቢዎችም ጭምር ስርጭቱ እየተስተዋለባቸው እንደሆነም በዘገባው ተጠቅሷል። ይህ ዓመት በተለምዶ የወባ ትንኝ እንዲራባ የሚያደርግ ወቅት ሲሆን ረዘም ያለ የሰኔ ወር ዝናብ መኖሩ ደግሞ ሁኔታውን በማባባስ ተላላፊ የሆነ በሽታ አምጪ ትንኞች የሚራቡበትን አካባቢ ምቹ እንዲሆን አድርጎታልም ተብሏል፡፡ የበሽታው ስርጭትም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም 40 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ የዩጋንዳ ጤና ሚኒስቴር በመግለጫው አክሏል፡፡ መንግስትም ዜጎች የወባ መከላከያ አጎበር መጠቀም መቀነሳቸውን በመጠቆም እ.አ.አ በ2017 የተሰራጩት አጎበሮችም ቢሆኑ እርጅና እየጀመራቸው ነው ሲል መናገሩን በመረጃው ሰፍሯል፡፡ መሰል የወባ ወረርሽኝ ለማስቆም ያግዝ ዘንድ የዩጋንዳ መንግስት ከየካቲት 2017 እስከ መጋቢት 2018 በመላ ሃገሪቱ ለሚኖሩ ዜጎች 38 ሚሊዮን የሚደርስ የወባ መከላከያ አጎበር ማሰራጨቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡ ቡሩንዲም ሌላኛዋ ምስራቅ አፍሪካዊት ሃገር ነች፤ በአሁኑ ወቅትም የወባ ወረርሽኝ በሽታን ለማስቆም እየተዋጋች ነው ሲል ዘገባው አስታውቋል፡፡ እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ከሆነ ካለፈው ጥር ጀምሮ ከተመዘገበው የ6 ሚሊዮን የወባ በሽታ ሪፖርት ውስጥ ከ1,800 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም