በኢነርጂ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ይሰራል _ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር

3474

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 በኢነርጂ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በጥናትና ምርምር ታግዞ ለመፍታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰራ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የዘርፉን ችግሮች ለመለየት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጨምሮ ከሌሎች በዘርፉ ጥናትና ምርምር ከሚያካሂዱ ተቋማትና ከተለያዩ የውጭ የግልና የመንግስት ተቋማት ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመለየትና ለመፍታት በምርምርና ጥናት መደገፍ ያለበት ቢሆንም የፋይናስና የሰው ኃይል እጥረት ማነቆ ሆኗል።

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፉን በጥናትና ምርምር በመታገዝ  በሚፈለገው ደረጃ  ለማሻሻል የፋይናንስ፣ የባለሙያ፣ የሰው ሃይል እጥረትና ሌሎች ተግዳሮቶች በስፋት ይስተዋላሉ።

እነዚህን ጨምሮ ሌሎች በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት፤ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎችን በዘርፉ በማሰማራት ለመስራት መታቀዱን ጠቁመዋል።

የሚስተዋለውን የባለሙያና የሰው ሃይል እጥረት ለማስተካከል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ለመስራት መታቀዱንም ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በውይይቱ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች በመለየት በቀጣይ ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ብለዋል።

ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዚሀ ውይይትም ችግሮችን መለየትና ወደ መፍትሄ መሄድ የሚያስችል ግብዓት እንደሚሰበሰብበት ጠቁመዋል።

ዘርፉ ላይ በርካታ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም የፋይናንስ፣ የባለሙያና የሰው ሃይል እጥረት የጎላ ችግር በመሆኑን በጥናትና ምርምር የታገዘ መፍትሄ ለማምጣት አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።

ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ማነቆ ናቸው ብለው የሚያነሷቸውን ጉዳዮች በማካተት በቀጣይ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በችግሩ ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም  ለባለሙያዎች ወቅቱን የጠበቀ ሙያዊ ስልጠና  በመስጠት ያለውን የሰው ኃይል ማነቆ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።