በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው–የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ

153

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 8/2011 በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ /አተት/ በሽታ ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ  የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ቱፋ እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት በአጎራባች ከተሞች የታየው የኮሌራ በሽታ ወደ ክልሉ መግባቱን ምልክት ታየቷል ።

የበሽታው ጥርጣሬ በታየባቸው 11 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ  በ6ቱ ሰዎች ላይ በሽታው ተገኝቷል ።

በሽታው የተከሰተባቸውን ስፍራዎች በመለየት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት በሽታው ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይዛመት የተቀናጀ የመከላከል ስራ እየተካሔደ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

በበሽታው ለተያዙ ሰዎችም በከተማና ገጠር ጤና ተቋማት ውስጥ በተዘጋጁ የህክምና ስፍራዎች ተገቢውን  ህክምናና ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ።

ህብረተሰቡ የአካባቢውንና የግል ንዕህናውን ከመጠበቅ ባሻገር አትክልትና ፍራፍሬን አጥቦ በመመገብና ውሃን አክሞ በመጠቀም የቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል ።

የበሽታው ምልክት ሲያጋጥም ወደ ጤና ተቋም በመምጣት አስፈላጊውን ህክምና በነጻ ማግኘት እንደሚቻልም  አቶ አሰፋ ተናግረዋል።

የኢሚር ኑር ወረዳ ጤና ጣቢያ ሃላፊ አቶ አብዱላዚዝ ሱፍያን በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከፍተኛ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርት የሚደርስበት በመሆኑ ህብረተሰቡ  አጥቦ እንዲጠቀምና  ጥሬ ስጋን አብስለው እንዲመገብ መክረዋል ።

የሐረዌ ጤና ጣቢያ ሐላፊ አቶ ጠሃ አብዶሽ  እንደገለፁት ወረዳው የበሽታው ምልክት ከታየባቸው አንዱ በመሆኑ  የበለጠ እንዳይስፋፋ ህብረተሰቡን በየመንደሩ የማስተማር፣ የመድሃኒትና የባለሙያ አቅርቦት የማጠናከር ስራ በቅንጅት እየተከናወነ  ነው ብለዋል ።