በአፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከነገ ጀምሮ ወደ ስፍራው ያቀናል

83
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 8/2011 በሞሮኮ በሚካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን አሸኛኘት ተደርጎለታል። ውድድሩ  ከነሐሴ 13 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባትና ካዛብላንካ ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን በ26 የስፖርት አይነቶች ከ54ቱ አፍሪካ አገራት የተወጣጡ ከ7 ሺህ በላይ ስፖርተኞች ይሳተፉበታል። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን በሂልተን ሆቴል አሸኛኘት ተደርጎለታል። በሞሮኮው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎዋ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስፖርተኛና የልዑካን ቡድን ታሳትፋለች። በ13 የስፖርት አይነቶች 188 ስፖርተኞች የሚሳተፉ ሲሆን በአጠቃላይ ከ250 እስከ 270 የሚሆን ልዑካን ቡድን ወደ ስፍራው ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል። ወርልድ ቴኳንዶ፣ አትሌቲክስ፣ ካራቴ፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ባድሜንተን፣ ክብደት ማንሳት፣ ቼስና ቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ መንግስት ለዘንድሮው የአፍሪካ ጨዋታዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሌላው ጊዜ በተለየ የተሻለ ዝግጅት እንዲደረግ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። ስፖርተኞቹ ላለፉት ሶስት ወራት ለውድድሩ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። "ባንዲራችሁ ክብራችሁ ነው" በማለት ለተወዳዳሪዎቹ መልእክት ያስተላለፉት ዶክተር አሸብር በጥንካሬ መንፈስ ውጤታማ ለመሆን በቡድን መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት በ11ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ከነበረው ፓራኦሊምፒክን ጨምሮ በ11 የስፖርት አይነቶች ተሳትፎ ዘንድሮው ወደ 13 ከፍ እንዲል ተደርጓል ብለዋል። ካራቴ ቅርጫት ኳስ እና ቼስ በሞሮኮው የአፍሪካ ጨዋታዎች የተጨመሩት የስፖርት አይነቶች ሲሆኑ ፓራኦሊምክ ራሱን ችሎ ብቻውን በጥር ወር 2012 ዓ.ም የሚካሄድ በመሆኑ በሞሮኮው ውድድር ላይ አልተካተተም። መንግስት ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በሞሮኮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አስፈላጊውን አቀባበልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል። ስፖርተኞች በብቃት፣ በውጤትና በስነ ምግባር ልቀው መገኛት እንደሚገባቸውና ባንዲራችንን ከፍ ለማድረግ በከፍተኛ የአገር ስሜት መወዳደር አንዳለባቸው አሳስበዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ አሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞች በውድድሩ በመሳተፋቸው ትልቅ ኩራት ሊሰማቸው እንደሚገባ ገልጻለች። ስፖርት የሰላምና ፍቅር መገለጫ አንደሆነና ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ይሄንን ስፖርታዊ እሴት በተግባር ማንጸባረቅ እንዳለባቸውም ተናግራለች። የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ዋና ሱፐር ኢንቴንዳንት ሁሴን ሽቦ ለሞሮ የአየር ጸባይ ተቀራራቢ በሚባሉ ቦታዎች ልምምድ እንደተደረገና ለውድድሩ የሚያስፈልገው አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል። የወርልድ ቴኳንዶ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ማርሸት ዘውዱ ስፖርተኞች ለሁለት ወራቶች በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ የሚያስፈለገውን ልምምድ ሲሰራ እንደቆየ ገልጻለች። በውድድሩ ከባለፉት ጊዜያት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚቻላቸውን እንደሚያደርጉም ቃል ገብታለች። በቀድሞ መጠሪያው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች አሁን ላይ የአፍሪካ ጨዋታዎች በሚል በሚካሄደው ውድድር የሚሳተፈው የልዑካን ቡድን በዙር ከነገ ጀምሮ ወደ ስፍራው ያቀናል። የአፍሪካ ጨዋታዎች(የአፍሪካ ኦሎምፒክ) የሚባለው ውድድር እ.አ.አ በ2020 በቶኪዮ ለሚካሄደው የአሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ እንደ ማጣሪያ ውድድር የሚያገለግል ነው። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2015 በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው በተካሄደው የ11ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በ7 ወርቅ  በ5 ብር በ10 የነሐስ ድምሩ 22 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ስምንተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች 7 ወርቅ ያገችበት ውድድር በአፍሪካ ጨዋታዎች ብዙ ቁጥር ያለው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ስድስቱ በአትሌቲከስ አንዱን በወርልድ ቴኳንዶ የተገኙ ናቸው። የአፍሪካ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ1965 በኮንጎ ብራዛቪል መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ11ዱም ውድድሮች ላይ የተሳተፈች ሲሆን በአጠቃላይ በውድድሮቹ 31 ወርቅ 39 ብር 52 ነሐስ በድምሩ 122 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። ግብጽ፣ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ እስካሁን በተካሄዱት 11 የአፍሪካ ጨዋታዎች ብዙ ሜዳሊያ በመሰብሰብ በቅደም ተከተል ከአንድ አስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም