በአዳማ ከተማ በመንገድ ብልሽት የትራፊክ መጨናነቅ እየተባባሰ ነው---አሽከርካሪዎች

70
አዳማ  ነሐሴ 8 /2011… በአዳማ ከተማ የአስፓልት መንገዶች  ብልሽት  የትራፊክ መጨናነቁነን  እያባባሰ መምጣቱን አሽከርካሪዎች ተናገሩ። የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት በበኩሉ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አሽከርካሪዎች እንዳሉት አዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞችም ሆነ ወደ ጅቡቲ ወደብ መተላለፊያ በመሆኗ የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ ሁኔታ ይስተዋልባታል። በተለምዶ ኤፍ.ኤስ.አር የተባለ አይሱዙ መኪና የሚነዳው አቶ ሰኢድ ሁሴን እንዳለው ከፍተኛ ጭነትና ኮንቴነር የተሸከሙ ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚመላለሱበት አውራ ጎዳናና የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገዶች ተደጋጋሚ ብልሽት ይስተዋልባቸዋል። በእዚህም አሽከርካሪዎች መንገድ መርጠው ለመጓዝ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመገልበጥ አደጋ የሚያጋጥምበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። “መንገዱ በመበላሸቱ ምክንያት እንደ ልብ መሄድ አልቻልንም፣ የመኪና እቃ በተደጋጋሚ እየተሰበረ ለወጪ ተዳርገናል፤ በእዚህም ተቸግረናል” ሲሉም ገልጿል። በየጊዜው የተሽከርካሪ አደጋ እንዲደርስ ምክንያት ለሆነው የመንገድ ብልሽት የሚመለከተው አካል ጥገና በማድረግ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ነው አቶ ሰኢድ የጠየቁት። በከተማው የባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪ ወጣት ያሬድ ወልዴ በበኩሉ በጎርፍና በመንገድ ብልሽት ምክንያት በከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ በየጊዜው እየተባባሰ መምጣቱን ተናግሯል። “የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ በመበላሸቱ ምክንያት ከቦታ ቦታ ፈጥኖ ለመጓዝ አልቻልንም” ያለው የባጃጅ አሽከርካሪው፣ ይህም በገቢያቸው ላይ ተጽዕኖ ከማድረሱ በተጨማሪ የባጃጁን ባሌስትራ በመስበርና ጎማውን በማበላሸት ለወጪ እንደዳረገው አስረድቷል። በከተማዋ በጥገና እጦት የተበላሹ መንገዶች በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከባድ ጭነት መኪና አሽከርካሪው አቶ አብዲ ጀማል ናቸው። “በየጊዜው ለአስፓልት መንገዶች የሚደረገው ጥገና በቂ ባለመሆኑ ስር ነቀል መፍትሄ ሊመጣ አልቻለም” ብለዋል የመንገዶቹ መበላሸት በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ እየፈጠሩ ያሉት ጫና እየተባባሰ መምጣቱ እየታወቀ ችላ መባሉ አግባብ አለመሆኑን ነው ያስረዱት። የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ደሜ በበኩላቸው አብዛኛዎቹ የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መበላሸታቸውን አምነዋል። እንደአቶ ብርሃኑ ገለጻ መንገዶቹ ለብልሽት የተዳረጉት ረጅም ጊዜ ከማገልገልና ከመንገድ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ነው። በተለይ ትላልቅ ተሽከርካሪዎች ለረጅም ሰዓት መንገድ ዳር በመቆምና መኪናቸውን በማሳጠብ አስፓልቱን ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራትን የሚፈጸምበት ሁኔታ መኖሩን ለአብነት አንስተዋል። የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅና የትራፊክ መጨናነቅ ችግርን ለማቃለል በተያዘው ዓመት አማራጭ መንገዶችን በማዘጋጀት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ መከልከሉን አስታውሰዋል። የተጎዱ የአስፓልት መንገዶችን ለመጠገን በተደረገው እንቅስቃሴም 7 ነጠብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መጠገኑን ተናግረዋል። “ከተፈቀደው ቶን በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ እንዳይቆሙ ከትራፊክ ፖሊስና ከትራንስፖርት አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው” ሲሉም ጠቁመዋል። “በከተማዋ ለጉዳት የተዳረጉ መንገዶች ተለይተው ዲዛይን እየተሰራላቸው ነው” ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ በ2012 በጀት ዓመት ከፍ ያለ በጀት በመያዝ ለማስጠገን መታቀዱን አስረድተዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም