የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ሰኔ 10 ቀን 2010 ይጀመራል

3220

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና በመጪው ሰኔ 10 ቀን 2010  በድሬዳዋ ከተማ ይጀመራል።

በሻምፒዮናው ላይ ከስድስት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወደ 200 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ አንጀሎ  እንደገለጹት የውድድሩ ዓላማ የስፖርቱ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ለመለካትና ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሥነ ምግባር ያላቸው የካራቴ ስፖርተኞችን ለማፍራት ነው።

በተጨማሪም ክልሎች በስፖርቱ ያላቸውን አቅም እንዲፈትሹና በካራቴ ስፖርተኞች መካከል የእርስ በርስ ትውውቅ ለመፍጠር እንዲሁም ልምድ ለመለዋወጥ ሻምፒዮናው ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

ሻምፒዮናው በሁለቱም ጾታዎች በ16 የውድድር ዓይነቶች የሚካሄድ እንደሆነም  ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ከነሐሴ 25 እስከ 28 ቀን 2010 በሚካሄደው የአፍሪካ ካራቴ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክለው ብሔራዊ ቡድን ከሻምፒዮናው እንደሚመረጥም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና እስከ ሰኔ 17 ቀን 2010 ይካሄዳል።

ካራቴ በዓለማችን በአንጋፋነታቸው ተጠቃሽ ከሆኑ የስፖርት ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ቻይና የስፖርቱ ምንጭ ናት።

የካራቴ ጥበብ በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንደ አንድ ስፖርት ተቆጥሮ ውድድሮች በሁሉም የዓለም ክፍሎች መደረግ መጀመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ጤንነትን ለመጠበቅ፣ ለአእምሮ እድገትና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋን ለመፍጠር እንደሚረዳ በመታመኑ ስፖርቱ በአጭር ጊዜ ተወዳጅነቱ እንዲልቅ አቅም ፈጥረውለታል።

ስፖርቱ በዓለም ደረጃ የተቀባይነቱ ደረጃ በቅብብሎሽ እየተጓዘ በመምጣት ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ እንደደረሰ ይነገራል።