የኢትዮጵያ የቱሪዝምና የባህል ስርጸት ማኅበር ተመሰረተ

1530

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 የኢትዮጵያ የቱሪዝምና የባህል ስርጸት ማኅበር በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና በዘርፉ ተቋማት ዛሬ በአዲስ አበባ ተመሰረተ።

”ማኅበሩ አገሪቱ በባህልና በቱሪዝም ዘርፍ የምታከናውናቸውን ሥራዎች ለማገዝና ለመደገፍ ሚናው የጎላ ይሆናል” ተብሏል።

በተለይም የአገሪቱን ቱባ የባህልና የቱሪዝም መስህቦች ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች በስፋት ለማስተዋወቅም እንደሚረዳም ተጠቅሷል።

የማኅበሩ ዳይሬክተር አቶ አስራት በጋሻው እንደተናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ጎብኚዎች ውስጥ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት በቁጥር  አነስተኛ ናቸው።

ለዚህም ዛሬ የተቋቋመው ማኅበር የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅና ጎብኚዎችን በመሳብ የላቀ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን እነዚህን የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችና መስህቦች ምጣኔ ኃብታዊ ሚናቸው ላይ በማተኮር አዎንታዊ ለውጦች ለማምጣት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የቱሪስት መስህቦችን ከማስተዋወቅና ቱሪስቶችን ከመሳን ጎን ለጎን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና መጤ የባህል ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ የሚደረገውን አገራዊ ጥረት ማኅበሩ የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በባህልና በቱሪዝም ሥራ ላይ አዎንታዊ ሚና የተጫወቱ ግለሰቦችና ተቋማትን ለማበረታታት ማህበሩ የእውቅናና የምስጋና መርኃ ግብር እንደሚያሰናዳ ጠቁመዋል።