የጋራ እሴት የሆነውን የልጃገረዶች ጨዋታ በዩኔስኮ የማስመዝገቡ ስራ ተጋምሷል

257
ነሐሴ 7/2011  ሻደይ፣ አሸንድዬና አሸንዳ የሚሰኘውና የሁለት ክልሎች የጋራ እሴት የሆነው የልጃገረዶችና ሴቶች ባህላዊ ጨዋታ በዓለም የማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል። በአማራ ክልል ዋግህምራ ሻደይ፤ በላስታ፣ ላሊበላና ጎንደር አሸንድዬ፤ በራያ ቆቦ ሶለል እንዲሁም በትግራይ ክልል እንደርታና ተምቤን አሸንዳ፤ በአክሱም አይኒዋሪና አዲግራት ደግሞ ማርያ ይሰኛል ጨዋታው። የዚህ የጋራ ባህላዊ እሴት በዩኔስኮ መመዝገብ የአማራና የትግራይ ክልሎችን ህዝቦች ይበለጥ የሚያስተሳስራቸው እንደሆነ ነው የተነገረው። ባህላዊ ጨዋታው በዓለም የማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ባለፈው መጋቢት 2011 ዓ.ም የምዝገባ ሰነዱ ለዩኔስኮ መላኩን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል። በኢትዮጵያ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ከ73 በላይ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማይዳሰሱ ባህሎች ቆጠራ ተካሂዷል። የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ ጥናትና ምርምር በማካሄድም ውጤቱ በህትመት ለተለያዩ አካላት መሰራጨቱን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በአገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ደረጃ ለማሳወቅና ለማስመዝገብ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ስራዎች የመስቀል ደመራ፣ ፍቼ ጨምበላላና የገዳ ስርዓትን ማስመዝገብ ተችሏል። በባለስልጣኑ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ደምረው ዳኜ የአገሪቷን ጥንታዊ ስልጣኔ እንዲሁም በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ይላሉ። የትግራይና የአማራ ክልሎች የልጃገረዶችና ሴቶች ባህላዊ ጨዋታ የሆነውን አሸንዳ፣ ሻደይና አሸንድዬ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። ባለስልጣኑም በክልሎቹ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች የጋራ እሴት የሆነውን የልጃገረዶች ጨዋታ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ለማስመዝገብ የተለያዩ ስራዎችን ከውኗል። ሰነድ በማዘጋጀት ሂደት ከክልሎቹ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በጋራ ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል። ከነሃሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የሚከወነው የአሸንዳ ሻደይና አሸንድዬ የሴቶችና የልጃገረዶች ጨዋታ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች አንድነትና ትስስር አጉልቶ እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል። እስካሁን ስለ በዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ ሁሉን የሚያስማማ ወጥ መረጃ ባይገኝም አንዳንድ መረጃ ሰጪዎች ከቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ የክረምቱን መውጣትና የበጋውን መምጣት በደስታ ለመቀበል የሚከበር መሆኑን ይገልጻሉ። በሌላ በኩል ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የተያያዘና በዓሉ በሚከወንባቸው አካባቢዎች የክርስትና እምነት ከተስፋፋ በኋላ የተጀመረ እንደሆነም ይነገራል። በባለስልጣኑ የቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው በዓሉ የአማራና የትግራይ ክልሎች ህዝቦች በተለያየ ስያሜ ቢያከብሩትም ተመሳሳይ ድርጊትና ዓላማ ያለው ነው ይላሉ። የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገባቸው አንዱ ባህል ከሌላው ይበልጣል ማለት አለመሆኑን ያወሱት አቶ ደሳለኝ ቁምነገሩ ባህሉን አስጠብቆ ለትውልድ ማቆየትና ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነም ያስረዳሉ። በሌላ በኩል የሚዳሰሱም ሆነ የማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ በኋላ ዩኔስኮ በየጊዜው ክትትልና ግምገማ የሚያደርግባቸው በመሆኑ ቅርሱን ጠብቆ ማቆየት ተገቢ መሆኑ ተገልጿል። የጥናትና ምርምር ዳይሬክተሩ አቶ ደምረው ዳኜ በተለይ የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ከመዝገቡ የሚያሰርዝ መሆኑን ነው የተናገሩት። የመስቀል ደመራ፣ ፍቼ ጨምበላላና የገዳ ስርዓት በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት የተመዘገቡ ናቸው። ዩኔስኮ የጥምቀትን በዓል በመጪው ህዳር 2012 ዓ.ም፣ አሸንዳ፣ ሻደይና አሸንድዬን ደግሞ በ2013 ዓ.ም እንደሚመዘግባቸው ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም