በአለም አቀፍ ደረጃ 3 ሺህ ታዳጊ ወጣቶች መከላከል በሚቻሉ ሁኔታዎች በየቀኑ እየሞቱ ነው -የአለም ጤና ድርጅት

112

ኢዜአ ነሃሴ 7/2011 የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው የአለማችን ወጣቶች ቁጥር ከምንግዜውም በላይ ጨምሯል ፤በዚህም ከአለማችን 7ነጥብ 2 ቢሊየን ህዝብ  3 ቢሊየን ያህሉ ከ25 አመት በታች መሆናቸው ነው የተነገረው ፤ይህም ከአለማችን ሀዝብ 42 ከመቶ ያህሉ ናቸው፡፡

ከነዚህ ወጣቶች 1ነጥብ 2ቢሊየን ያህሉ እድሜያቸው ከ10 -19 መሆኑም ታውቋል፤የአለም ጤና ድርጅት ይህን የወጣትነት ግዜ የህይወት ትልቁ የፈተና ግዜ ብሎታል፡፡

ይህ እድሜ ሰዎች ግለኝነትን የሚያዘወትሩበት፣አዲስ ግንኙነት የሚመሰርቱበት፣ማህበራዊ ክህሎት የሚያዳብሩበት እና በቀሪው ህይወታቸው የሚመሩበትን ክህሎት የሚያገኙበት ነው፡፡

እኤአ በ2016 ብቻ በየቀኑ  3 ሺህ ወጣቶች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የገለፀው የሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ እድሜያቸው ከ10 -19 ያሉ 1.1 ሚሊየን ታዳጊ ወጣቶች መከላከል በሚቻሉ ሁኔታዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ፤የትራፊክ አደጋዎች፣ከእርግዝና ጋር የሚከሰቱ ውስብስብ ችግሮች ፣ ወሊድ እና ኤች አይቪ ኤድስ ለሞታቸው ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡

“የታዳጊ ወጣቶች በተለይም ሴቶቹ ላይ ጤናና ደህንነታቸው ላይ መስራት በአለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ፖሊሲ አውጪዎች ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር ነው፤ ወጣቶች ላይ የሚሰራው ስራ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው በአለም አቀፍ ደረጃ የጠቀመጡ ዘላቂ የልማት ግቦችንም ለመድረስ ያግዛል” ያሉት የተባበሩት መንግስታት የስነህዝብ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ናታሊያ ካነም ናቸው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የጤና ኤጀንሲ በበኩሉ ወጣቶች የሚገጥማቸው አብዛኞቹ የጤና ችግሮች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ፣ግጭቶችና የአለማችን መጨናነቅ፣ከተሜነትና ተንቀሳቃሽነት የፈጠራቸውየትራፊክ አደጋዎች መሆናቸውን አሳውቋል፡፡

በተጨማሪም በኢንተርኔትና በሚዲያ አማካኝነት ወጣቶች ስለ ትምባሆና ስለ አደገኛ እፆች ያላቸው ተጋላጭነት መጨመሩ፣ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ ጤነኛ ያልሆኑ ምርቶች መብዛት ወጣቶችን ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረትና እድገታቸውን ሳይጨርሱ ለአደገኛ ሁኔታዎች እንዲጋለጡ አድርጓል ተብሏል፡፡

የአልኮልና የትምባሆ ሽያጭን የሚከለክሉ ህጎች ቢወጡ እንኳን ለተፈፃሚነታቸው የቤተሰብና የማህበረሰቡ ትብብር ወሳኝ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

ወጣቶች ለወሲብ ቀስቃሽ ምስሎች ተጋላጭ መሆናቸው ስለስለግብረ ስጋ ግኝኙነት በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸውና የሚገጥማቸውን ችግር ሳያጤኑ ለአደጋ የሚጋለጡበት ሁኔታም እንዳለ ነው የተመለከተው፡፡

ወጣቶች በሃላፊነት ህይወታቸውን እንዲመሩ በቤት ውስጥና በትምህርት ቤቶች ማስተማር እንደሚገባ የገለፀው ዘገባው ወጣቶች ጤና ላይ መስራት አስቸኳይ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት አስምሮበታል ብሏል፡፡

ሆን ብሎ እራስን መጉዳት እድሜያቸው ከ15-19 ላሉ ወጣቶች ሞት በሶስተኝነት ደረጃ የሚጠቀስ መሆኑን ያመለከተው ዘገባው 80 ከመቶ የድብርት ስሜት በወጣትነት እንደሚጀምርና ችግሩ ሳይለይና ሳይታከም እንደሚቆይ አመላክቷል፡፡

“ከአለማችን 40 ከመቶ ህዝብ እድሜው ከ24 አመት በታች እንደመሆኑ አለማችን እየገጠማት ላለው ችግር መፍትሄ ለመሻት እነሱ ላይ መስራ ያስፈልጋል፣መብታቸውም ነው ፤ለወጣቶችም ትርጉም ያለው ፣ደህንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ የጤና አገልግሎትን ማድረስና ዘላቂ ልማት ለአባል ሃገራት ለነገ የማይባል ተግባር ነው፣ለዚህም የአለም ጤና ድርጅትና አጋሮቹ እንዲሁም ወጣቶች ጭምር ሃላፊነት አለባቸው” ያሉት በአለም ጤና ድርጅት  ከቤተሰብ፣ሴቶችና ህፃናት ዲፓርትመንት ዶክተር ሺያማ ኩሩቪላ ናቸው፡፡