ቻይና በትምህርት ዘርፍ ከአፍሪካ ጋር የምታደርገውን ትብብር አጠናከራ ትቀጥላለች - በኢትዮጵያ ቻይና አምባሳደር

44
ነሐሴ 7/2011  የቻይና መንግስት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ አገራት ጋር በትምህርት ልማት ዘርፍ ያለውን የትብብር ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ተናገሩ።
በአሁኑ ወቅት 600 ኢትዮጵያውያን የሁለተኛና ሶሰተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በቻይና  የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተከታተሉ ነው።
ቻይና ለአፍሪካ አገራት ነፃ የትምህርት እድል በመስጠት በስፋት ትሰራለች።አገሪቱ ነጻ የትምህርት መርሃ ግብሩን የጀመረችው እ.ኤ.አ ከ1956 ጀምሮ ሲሆን ቁጥሩ በየአመቱ እያደገ መጥቷል። በተለይም እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ ቻይና በየአመቱ ለ10 ሺህ አፍሪካዎያን ነጻ የትምህርት ዕድል እየሰጠች ትገኛለች። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያንም በየዓመቱ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው። በዚሁ መርሃ ግብር መሰረት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2019/2020 በቻይና ነጻ የትምህርት ዕድል ላገኙ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ የሽኝት መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የቻይና መንግስት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ለተውጣጡ 31  የሁለተኛና ሶሰተኛ ዲግሪ ነው ነፃ የትምህርት እድል የተሰጠው። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ታን ጃን በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የአፍሪካውያን ነጻ የትምህርት ዕድል በቻይና ትኩረት የሚሰጠውና ትርጉም ያለው መርሃ ግብር ነው። በመሆኑም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ከምትተገብራቸው የትብብር መርሃ ግብሮች መካከል የትምህርት ልማት ዘርፉ ቀዳሚው መሆኑን አምባሳደሩ ገልፀዋል። በማደግ ላይ ላሉ አገራት ዕድገት ትምህርት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ መንግስታቸውም  ለእዚህ አገራት በዘርፉ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የ2019/2020 ነጻ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የሆኑት ኢትዮጵያውያንም የአገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ድልድዮች እንዲሆኑም መክረዋል። አምባሳደሩ እንደገለጹት ወደቻይና የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ለወንጀል ከሚያጋልጧቸው ድርጊቶች ራሳቸውን በመጠበቅ ሊጠነቀቁና ለቻይና ህጎች ተገዢ ሊሆኑ ይገባዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የቻይናና ኢትዮጵያ ትብብር በተለይም በትምህርት መስክ እየተጠናከረ የመጣው ትብብር ወደፊትም እንደሚቀጥል እምነታቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ወደ600 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በሁለተኛና ሶሰተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በቻይና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛል ብለዋል። በኤሌክትሮኒክ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት መስኮችም 200 ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በኢትዮጵያ መንግሰት የገንዘብ ድጋፍ በቻይና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም አክለዋል። ለትምህርት ወደቻይና የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚወክሉ መሆናቸውን በመገንዘብ የህገ-ወጥ ስራ አካል እንዳይሆኑና አገራቸውን በመልካም ስም እንዲያስጠሩ ዶክተር ሳሙኤል  አሳስበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም