የአማራ ክልል ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሰላማዊነት ትኩረት እንዲሰጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ

114
ነሀሴ 7 /2011 በአማራ ክልል የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የ2012 የትምሀርት ዘመን ለመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊነት ትኩረት እንዲሰጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ። ክልል አቀፍ የትምህርት ንቅናቄ ኮንፈረንስ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ተቋማት ህጻናትና ውጣቶችን በዕውቀት፣ ክህሎትና በሥነ ምግባር በማነፅ የልማትና የዴሞክራሲ ለውጦችን ማስቀጠል ይገባቸዋል። ተቋማቱ የእውቀትና በስነ ምገባር የታነፀ ዜጋ ለማፍራት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማስፈን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዘበዋል። በመጪው የትምህርት ዘመን በየደረጃው ባሉ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ተቋማቱና የባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። "በተጠናቀቀው ትምህርት ዘመን በክልሉ በሚገኙ ከ9ሺህ በላይ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተስተናግደዋል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ናቸው። በቀጣዩ ትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በየደረጃው መማር የሚገባቸውን ህጻናትና ወጣቶች ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ተቋማቱ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል ። ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በአንደኛ ደረጃ የሚያስተምሩ የሰርተፊኬት መምህራንን በዲፕሎማ ደረጃ ማስመረቁን አስታውሰዋል። መምህራንን የስልጠና ደረጃ ማደጉ በእውቀትና በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ለማፍራት አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል ። ኮንፈረንሱ እስከ ነሐሴ 9 ቀን 2011 ይቆያል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም