በዞኑ ከ203 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሰሊጥ እየለማ ነው

59
ጎንደር (ኢዜአ) ነሀሴ 7 ቀን 2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ203 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሰሊጥ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የሰሊጥ ልማቱ እየተከናወነ ያለው በባለሀብቶችና በአርሶ አደሮች አማካኝነት ነው። ልማቱ የውጭ ገበያን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑም የተሻሻለ የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም እየተካሄደ ነው፡፡ በሰሊጥ ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ 120 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑንም አመልክተዋል። በሰሊጥ ከለማው መሬት ውስጥ 87 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው በዘርፉ በተሰማሩ ባለሃብቶች እየለማ ሲሆን ቀሪውም በአርሶ አደሮች የሚለማ መሆኑን ታውቋል። “በሰሊጥ ከተሸፈነው ማሳም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃልም” ብለዋል ባለሙያው፡፡ አቶ ሞገስ እንዳሉት በምርት ዘመኑ የሰሊጥ ምርጥ ዘር እጥረት በማጋጠሙ አርሶ አደሩ የአካባቢውን ዘር አበጥሮ እንዲጠቀም ተደርጓል። በመተማ ወረዳ የሽመለ ጋራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አቶ አበራ ማስረሻው እንዳሉት ካላቸው 10 ሄክታር መሬት ውስጥ በ7 ቱ ላይ ሰሊጥ እያለሙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የሰሊጥ ምርጥ ዘር ተጠቅመው ለመዝራት ቢያቅዱም ምርጥ ዘር ማግኘት ባለመቻላቸው የአካባቢ ዘር ለመጠቀም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ የዚህ ዓመት የዝናብ መጠን ለሰሊጥ ማሳ ተስማሚ በመሆኑ እስከ 50 ኩንታል አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁም አስታውቀዋል፡፡ በቋራ ወረዳ በሚገኘው ቁጥር 4 የእርሻ ልማት ላይ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ገነቱ ጋሻው በበኩላቸው ካላቸው 40 ሄክታር መሬት ውስጥ 28 ሄክታሩን በሰሊጥ የሰብል ዘር መሸፈን እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ በምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ምክንያት ለመጠቀም ካሰቡት 80 ኪሎ ግራም ምርጥ ዘር ውስጥ ማግኘት የቻሉት 25 ኪሎ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ገነቱ፣ ለምርት ማሳደጊያ የሚውል ሦስት ኩንታል ማዳበሪያ መጠቀማቸውንም አመልክተዋል፡፡ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በግብርና ባለሙያ ምክር ታግዘው እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በዚህ የምርት ዘመን በተለያዩ ሰብሎች በአጠቃላይ 370 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሰራ ሲሆን እስካሁንም 340 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱ ታውቋል። በአጠቃላይ ከሚለመው መሬትም 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንመምሪያው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም