ከማዕከላት የሚወጡ የሰብልና ጥራጥሬ ዝርያዎች ምርትና ምርታማነታችንን አሳድገውልናል-የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች

113
ጎባ ነሐሴ 7 ቀን 2011 ከግብርና ምርምር ማዕከላት የሚወጡ የተሻሻሉ የሰብልና ጥራጥሬ ዝርያዎች መጠቀም ምርትና ምርታማነታቸውን ከእጥፍ በላይ እንዳሳደጉላቸው በባሌ ዞን የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡ የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናና ምርታማነትን ለመጨመር የጥራጥሬና የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረግኩ ነው ብሏል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት ምርታማነታቸው ያደገው በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ከዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችጋር አጣምረው በመጠቀማቸው ነው። የሰልቃ ቀበሌው አርሶ አደር ሁሴን ሐጂ አደም እንዳሉት ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር የአካባቢ ዝርያ የሚያገኙት ምርት ከ10 ኩንታል የማይበልጥ እንደነበር ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ከማዕከሉ ያገኙትን ምርጥ ዝርያ በሙሉ የግብርና ፓኬጆች በመተግበር ስንዴ በሄክታር ከ70 እስከ 80 ኩንታል በማምረት በሕይወታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በበልግ ወቅት በአምስት ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ስንዴ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አቶ ሁሴን አስታውቀዋል፡፡ የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ ዝርያዎችን በቅርበት እንድናገኝ ከማድረግ ባሻገር፤ ምርታማነትን ከሚጨምሩ የግብርና አሰራሮች ጋርም እንድተዋወቅ ረድቶኛል ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ታጁ አብዱልቃድር ናቸው ። ''በዚህ ዘዴ በሄክታር የማገኘውን ስንዴ ምርት ከ15 ወደ 65 ኩንታል ማሳደግ ችያለሁ'' ብለዋል። ሌሎች አርሶ አደሮችም ከማዕከሉ የሚለቀቁ ዝርያዎችንና የግብርና አሰራሮችን የባለሙያ ምክር በመጠቀም ጋር ቢተገብሩ  ምርታማ  ይሆናሉ ሲሉም ይመክራሉ። ማዕከሉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የጥራጥሬና የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት በማዕከሉ የቅባትና እና ጥራጥሬ ሰብሎች ቡድን መሪና ተመራማሪ አቶ ጋሻው ሰፈራ ናቸው ፡፡ ማዕከሉ በዚህ ዓመት በሽታንና ተባይን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ሁለት  የቦሎቄ፣  አንድ  የሽምብራና  አንድ የስንዴ ዝርያዎች መልቀቁን አስታውቀዋል። ዝርያዎቹ በብሔራዊ የዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ተገምግመው ከሰኔ  2011 ጀምሮ መለቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ዝርያዎቹ ለሰባት ዓመታት በምርምር መቆየታቸውን የተናገሩት ተመራማሪው፣ ''የቦሎቄው ዝርያ  በሄክታር  በአማካይ ከ13 እስከ 25 ኩንታል፣ ሽምብራው ከ29 እስከ 46 ኩንታል ሲሆን፣ የስንዴ ዝርያው ከ49 እስከ 59 ኩንታል ምርት ይሰጣሉ'' ብለዋል። በሄክታር የሚገኘው ምርት መጠን ከነባር ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸር ከ19 እስከ 63 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡ የስንዴ ዝርያው ከነባሩ በሽታ በመቋቋም የተሻለና በምርታማነት ረገድም ከ23 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ''በተለይ የቦሎቄ ዝርያዎቹ በዓለም ገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት ስላላቸው አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር የሆነ ምርት በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል'' ብለዋል፡፡ ዝርያዎቹ በባሌ ዞን ቆላ፣ ወይና ደጋ፣ ደጋናና ተመሳሳይ ሥነ  ምህዳር  ባላቸው የአገሪቱ  አካባቢዎች  ተሞክረው ተስማሚነታቸው  መረጋገጡንም አስረድተዋል፡፡ የሲናና ግብርና ምርምር ማሰዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ በሪሶ እንዳስታወቁት ማዕከሉ በጥራጥሬና በቅባት እህሎች ዘርፍ አሁን የለቀቃቸውን ሳይጨምር 20 የምርምር ውጤቶች ለተጠቃሚው አድርሷል፡፡ ቴክኖሎጂ ማፍለቅ ብቻውን ግብ አለመሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በምርምር የሚወጡ ዝርያዎች አባዝቶ ለአርሶ አደሮችና በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ ባለሀብቶች ተደራሽ ለማድረግ ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ  ጋር  ተቀናጅቶ በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስከያጅ አቶ ገብረወልድ ኪዳኔ በበኩላቸው ከምርምር ተቋማት በየጊዜው የሚያወጡትን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቀበልና በማባዛት  የምርጥ ዘር አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ አሁን በምርምር የተገኙት የጥራጥሬ ዝርያዎች የአርሶ አደሩን ዘንድ ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡ የሲናና ምርምር ማዕከል በ1978 ከተቋቋመ ወዲህ 72 በምግብ እህል፣ በጥራጥሬና በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ የምርምርው ጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም