የተከልናቸውን ችግኞች ለፍሬ ለማብቃት እንየሰራን--የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪዎች

62
ፍቼ ነሐሴ 7 / 2ዐ11 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪዎች የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባክቦ ለፍሬ ለማብቃት ጥረት እያደረግን ነው አሉ። ኅብረተሰቡ ዘንድሮ  ለተተከሉ ከ15ዐ ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንዲንከባከብ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት በተያዘው የክረምት ወቅት የተከሏቸውን ችግኞች በማጽደቅ ለተፈለገው ዓላማ ለማዋል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው። የወርጡ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አክሊሉ ረጋሳ በቅርቡ የተከሏቸው አገር በቀል ችግኞች እንዲፀድቁ የኩትኳቶና  የአፈር ድጋፍ ሥራዎች በቋሚነት እያከናወንኩ ነው ብለዋል። በተለይም በክረምት ወቅት ችግኞቹ የተተከሉባቸው ቦታዎች ውሃ እንዳይቋጥሩና ሥሩ እንዳይበሰብስ አፈር በማስታቀፍ  ክትትል እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፋናዬ በቀለ በበኩላቸው የተከሏቸው የማገዶ ዛፎች ከሶስት አሰከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ፀድቀው ለውጤት እስኪበቁ እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ችግኞቹ በእንሰሳት እንዳይበሉ የክለላና የአጥር ሥራ  ከማከናወን በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም እያሳደጉ  መሆኑንም ተናግረዋል ። በቶርባን አሼ ቀበሌ ከ5ዐዐ በላይ አገር በቀል ችግኞችን በወልና በጋራ መሬት ተክለው እየተንከባከብኩ ነው የሚሉት አቶ ሞቱማ ጋሪ ናቸው፡፡ በተለይ ችግኞቹ የተተከሉባቸው  ቦታዎች ውሃ እንዳያዝልና አፈሩ እንዳይሸረሸር እያደረግኩ ነው ብለዋል፡፡ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በቀለ ባዬቻ የተከሏቸውን ከ2ዐዐ በላይ የፍራፍሬ ችግኞች ለማጽደቅ  በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ የክብካቤና የድጋፍ ሥራውን በበጋ ወቅትም እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል፡፡ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ከበደ ኅብረተሰቡ በዞኑ 13 ወረዳዎች የተተከሉትን  ችግኞች በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ እንዲያስተላልፍ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ካለፈው ወር አጋማሽ  ጀምሮ በመሰጠት ላይ ያለው የችግኝ የጥበቃና ክብካቤ ትምህርት ከ27ዐሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ነው ብለዋል፡፡ ትምህርቱን ባለሙያዎችና በጐ ፈቃደኛ ወጣቶች በተለይም ለአርሶ አደሮች የሚሰጡት ሕዝብ በብዛት በሚገኙባቸው መድረኮች እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ እስካሁንም ከ100ሺህ በላይ ሕዝብ ትምህርቱን መከታተሉን  አቶ ፍቅሩ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከሉትን 12 ሚሊየን  ችግኞች ለማጽደቅ የተጀመረው እንክብካቤ አበረታች እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ችግኞቹ ሙሉ ለሙሉ እንዲፀድቁ ከመንከባከብ ባሻገር፤ገጠሩን ለማልማትና ከተሞችን ማፅዳት የዕለት ተእለት ሥራቸው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሀብቶም በቀለ ናቸው፡፡ በአረንጓዴ ልማት የአሻራ ቀን ሁሉን አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመከናወኑ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አመርቂ  እንደነበርም  ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም