በበዓሉ አቅም የሌላቸውም ይታሰባሉ

61
ነሀሴ 5/2011 የኢድ አል አድሃ በዓል የመስዋዕትነት በዓል በመሆኑ ደሃ የማይሳተፍበት ኢድ ተቀባይነት እንደሌለው የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ። የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በሰላማዊ መንገድ ማክበር የተቻለው ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሰላም ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል። የእምነቱ ተከታዮች የተራበ በማብላትና የተጠማ በማጠጣት በዓሉን አቅም ከሌላቸው ድሆች ጋር ያከብሩታል። በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ወጣት አዱኛው ሙጬ ለኢዜአ እንዳለው፤ የኢድ አል አድሃ በዓል የመስዋዕትነት በዓል ነው። በመሆኑም ኢዱ የተባረከ ይሆን ዘንድ የእስልምናም ሆነ የሌላ እምነት ተከታይ ከሆኑ ድሆች ጋር በጋራ መከበር አለበት። ወጣቶች ራሳቸውን ከነውጥና ሁከት በማራቅ አላህ በሚያዝዘው መሰረት ለአንድነትና ለትብብር መስራት ይጠበቅብናል ነው ያለው። የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሚል ጠሃ የኢድ አል አድሃ በዓል አንዱ እየበላ ሌላው ፆም የሚያድርበት ጉዳይ መኖር እንደሌለበት የሚያስተምር መሆኑን ይገልፃሉ። በመሆኑም ትክክለኛ የኢድ አል አድሃ በዓል ተከበረ የሚባለው የተቸገሩትን በመርዳት፤ በአብሮነትና በትብብር መሆን አለበት ብለዋል። በዓሉ አንዱ ተክዞ ሌላው የሚደሰትበት ሳይሆን ሁሉም በጋራ ለዓለም ሰላም አንድነትና አብሮነት የሚሰበክበት መሆኑንም ጠቁመዋል። ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ ሀሰን አብዲ በበኩላቸው በዓሉ በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም መትጋት አለባቸው ነው ያሉት። የሰላም ዋጋ ቀላል አይደለም ያሉት አቶ ሀሰን አብዲ፤ ሶሪያዊያን ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት በድህነት ሳይሆን በሰላም እጦት መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። ሰላም ኃይማኖት፣ ዘርና ቀለም ሳይለይ የጋራ ትብብርና አንድነትን እንደሚጠይቅ በመረዳት ለሰላም ዋጋ እንከፍላለን ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም