በጉጂ ዞን ከ48 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፈነ

90
ነጌሌ ነሐሴ 5 /2011 በጉጂ ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ከ48 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በግብርና ባለሙያዎችና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የመኽር አዝመራ ምርታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አንዳንድ አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡ በጉጂ ዞን በዘንድሮው የመኽር አዝመራ 82 ሺህ 725 ሔክታር መሬት ታርሶና ለስልሶ የተዘጋጀ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ 48 ሺህ 163 ሔክታር መሬት በዋና ዋና ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል ፡፡ በአዝመራው በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ 65 ሺህ የዞኑ አርሶአደሮች መካከል 5 ሺህ ሴት አርሶአደሮች ናቸው ብለዋል ። በሻኪሶ ወረዳ የመጋዶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አየለ ኤሌማ በሰጡት አስተያየት የምርት ማሳደጊያዎችን በመጠቀም ለመኽር አዝመራ ካዘጋጁት ሁለት ሄክታር መሬት እስካሁን ግማሹን በገብስና በጤፍ ዘር ሸፍነዋል፡፡ በልማት ጣቢያ ሰራተኞች እየተደረገላቸው ባለው የሙያ እገዛ በመስመር እንዲዘሩና የተመጣጠነ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲጠቀሙ በመደረጉ ከአዝመራው 40 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብም አቅደዋል፡፡ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ወዴሳ በቀለ በበኩላቸው ለመኽር አዝመራ ካዘጋጁት አብዛኛውን መሬት በዘር መሸፈናቸውንና እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ የዘር ስራቸውን እንደሚያጠናቅቁ ጠቁመዋል፡፡ በመኽር አዝመራው ስምንት ኩንታል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመጠቀም ለማልማት ካቀዱት አራት ሔክታር መሬት እስከ 75 ኩንታል ምርት ለመሰበሰብ ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም