ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የመቻቻልና የመከባበር እሴቱን በማጎልበት ለአገራዊ አንድነቱ መጠናከር መስራት አለበት

101

ጋምቤላ  ነሐሴ  / 2011 ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ያለውን የመቻቻልና የመከባበር እሴቱን በማጎልበት ለአገራዊ አንድነቱ መጠናከር እንዲሰራ የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጠየቁ፡፡

1440ኛው የአረፋ /ኢድ አል አድሃ/ በዓል ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ሐጂ ዑመር ሽፋ በበዓሉ ላይ  እንደተናገሩት ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የመቻቻል፣የመከባበርና የመተሳሰብ እሴቱን በማጠናከር ለአገሪቱ ሰላምና ልማት መስራት አለበት፡፡

በተለይም ከሀይማኖት አስተምሮ ውጭ የሆኑ የዘረኝነትና የአክራሪነት ዝንባሌዎችን መታገል ለአንድነቱ መቆም  ይገባዋል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር ለሌላቸው በማካፈልና ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር የቆየውን አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሃይማኖቱ ተከታዮች በሰጡት አስተያየት በዓሉን ሲያከብሩ እምነቱ በሚፈቅደው መልኩ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሁሴን አህመድ የተባሉ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት በዓሉን ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን በተለይም እምነቱ የሚፈቅደውን አብሮ በመብላትና አንድነታቸውን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ የቆየውን ኢትዮጵያዊ አንድነት በሚያጎለብት መልኩ በዓሉን ሊያሳልፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

“በዓሉን ስናከብር ሃይማኖቱ እንደሚያስተምረው ያላቸው ለሌላቸው አንድ ሦስተኛውን በማካፈል፣የተቸገሩትን በመርዳት፣የተራቡት በማብላትና በሌሎችም በጎ እሴቶች መሆን አለበት” ያሉት ደግሞ አቶ ሠይድ አሊ ናቸው፡፡

ኢማም ዛኪር ኢብራሂም የተባሉ የሃይማኖት አባት በበኩላቸው በዓሉን ስናስብ ለአገራዊ አንድነትና ለሕዝቡ አብሮነት መጠናከር የሚሰራበት በዓል ልናደርገው ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይም በዓሉ አባቶቻችን ያቆዩትን የመቻቻል፣የመከባበር፣የመደጋገፍ እንዲሁም አብሮ የመኖርና ሌሎች እሴቶችን በሚያጠናክር ሁኔታ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በተመሳሳይ ሁኔታ በሐረሪ ክልልና ከተማና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን 20 ወረዳዎችና አራት ከተሞች ተከብሯል።