ኦቲዝም ያለባቸው ልጆቻቸው ዕጣ ፈንታ ያስጨነቃቸው ወላጆች አግዙን ይላሉ

71
ነሃሴ 5/2011 ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ቤተሰቦች የልጆቻችን የወደፊት እድል ፈንታ ያስጨንቀናልና ያገባናል ብላችሁ አግዙን ብለዋል። እነዚህ ወላጆች የትምህርት እድል ካገኙት ባሻገር ለዘመናት በቤት ውስጥ የተዘጋባቸውን ልጆች ወደ ብርሃን ለማውጣት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። አቶ እስራኤል መንግስቱ ኦቲዝም ያለበት የዘጠኝ ዓመት ልጅ አባት ናቸው፤ የጤና እክሉ በልጃቸው ላይ መታየት የጀመረው ዕድሜው ሁለት ዓመት ተኩል ካለፈው በኋላ መሆኑን ይናገራሉ። ልጃቸው ኦቲዝም እንዳለበት የተመለከቱ የአካባቢያቸው ነዋሪዎች "በሃጢያት ምክንያት የመጣ ቁጣ" በመሆኑ ወደ ቤተ እምነት ሄደው አምላካቸውን እንዲማፀኑ መከሯቸው። እርሳቸውም የልጅ ነገር ነውና ወደተለያዩ የእምነት ቦታዎች በመሄድ መፍትሄ ቢሹም አልተሳካላቸውም። “ከአካባቢዬ በመራቅ የተሻለ አመለካከት አላቸው ብዬ ወደገመትኳቸው ሁለት ቦታዎች ብሄድም እዛም የተሻለ አመለካከት ያለው ሰው አላገኘሁም” ይላሉ አቶ እስራኤል ። ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው በመመለስ የገጠማቸውን ችግር በፀጋ ተቀብለው ኑሯቸውን እየገፉ ሳለ ልጃቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዳለባቸው በማሰብ ቢልኩትም ከወራት የዘለለ ሳይማር ‘ተማሪዎችን እየረበሸ ነው’ ተብለው በተደጋጋሚ ወደ ቤት እንዲወስዱት ተደርገዋል። አሁን ልጃቸው ህክምና እየተከታተለ ለውጥም እያሳየ መሆኑን የሚገልፁት አቶ እስራኤል ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ትምህርት እንዲያገኙ ከእያንዳንዱ የአገሪቱ ሀብት በፍትሀዊነት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ይላሉ። ኦቲዝምን በተመለከተ አሁን ላይ የተሻለ ነገር መኖሩንና የችግሩ ሰለባ የሆነችው የ31 ዓመቷ ልጃቸውም ለውጥ እያሳየች መሆኗን የሚናገሩት ወይዘሮ ታደለች ገብረሚካኤል ናቸው። ወይዘሮዋ እሷን በወለዱበት ጊዜ ልጃቸውን የሚያስተምሩበት ማግኘት ቀርቶ ጥቃት ታደርስብናለች በሚል ፍራቻ የቤት ሠራተኛ በማጣታቸው ለአምስት ዓመታት ስራ ለማቆም መገደዳቸውን ያስታውሳሉ። አሁን ልጃቸው በአፄ ልብነ ድንግል የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ባገኘችው ስልጠና በመታገዝ በዶሮ ማርባት ስራ መሰማራቷን ተናግረዋል። የኀብረተሰቡን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየርና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ልጃቸው ኦቲስቲክ እንደሆነ ሲያውቁ ተደናግጠው ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንኳን ባለማወቃቸውም ተቸግረው እንደነበረ የገለፁት ደግሞ አቶ ዘካሪያስ ገብረእግዚአብሔር ናቸው። “ይህን ነገር መቀበል ፈተና ነበር” ያሉት ወላጅ ራሳቸውን ካሳመኑ በኋላ እንኳን ልጃቸውን የት እንደሚያቆዩ ማሰብ ሌላ ችግር እንደነበር አውስተዋል። ከሶስት ዓመታት ጥበቃ በኋላ ልጃቸው ጆይ ኦቲዝም ማዕከል እንደገባና አሁን ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ እንደጀመረ ነው የገለፁት። “በየቤቱ በርካታ ልጆች በር ተዘግቶባቸው አሉ” የሚሉት አቶ ዘካሪያስ እነዚህን ልጆች ወደ ብርሃን ለማምጣት ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የኪዩር ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አይዳ አባተ በበኩላቸው ወንድማቸው ኦቲስቲክ በመሆኑ ሆስፒታል ሄዶ መታከም እንደሚፈራ ይናገራሉ። ሆስፒታል ውስጥ በመስራታቸው ወንድማቸውን እንዲታከም እንደሚያደርጉና በሚሰሩበት ሆስፒታልም ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች ቅድሚያ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በሌሎች ሆስፒታሎችም ይህ ነገር መለመድ እንዳለበት ምክራቸውን ለግሰዋል። ወላጆች “ለምን እኔ ላይ ሆነ” ከሚል አስተሳሰብ በመውጣት “ለምን እኔ ላይ አይሆንም” የሚለውን ማየት አለባቸው ያሉት ደግሞ የኒያ ፋውንዴሽን መስራችና ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ናቸው። “ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ክፉ የማይሰሩ፣ መጥፎ የማይናገሩ ናቸው” ያሉት ወይዘሮ ዘሚ “ልጆቻችንን ውደዱልን፣ አክብሩልን፣ የሚገባቸውን ስጡልን” ሲሉ ጠይቀዋል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሁሉም ኀብረተሰብ እኩልና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲሰጡም ጠይቀዋል። የማዕከሉ የስነ-ልቦና አማካሪ አቶ ሄኖክ ኃይሉ ማዕከሉ ለወላጆችና እናቶች ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ እየሰራን ነው ብለዋል። በጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ልዩ አማካሪ አቶ ኢሳይያስ መለሰ ሚኒስቴሩ ኦቲዝም ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ። በጤና በኩል ልዩ ፍላጎት ያላቸውን የኀብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በሌሎች ዘርፎችም ይህ ስራ እንዲጠናከር ‘ብሔራዊ የኦቲዝም ካውንስል ተቋቁሞ ቢሰራ’ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ወይዘሮ ዘሚ የኢትዮጵያ ኦቲዝም ሶሳይቲ ተጠናክሮ የማስተባበር ስራውን በዋናነት እንደሚቀጥል ገልጸው ወላጆች ፀጋዎቻቸው የሆኑትን ልጆቻቸውን መብት ለማስጠበቅ እንዲሞግቱ ሲሉም አሳስበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም