አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው

67
ኢዜአ ነሀሴ 3/2011  አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ገለጸ። ኮርፖሬሽኑ በፓርኮች ግንባታና ምርት ዙሪያ ከምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የሙያ ማህበራት ጋር ተወያይቷል። ውይይቱ በኢትዮጵያ በመስኩ እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ፣ እየተገኙ ያሉ ውጤቶችና ችግሮች ላይ ያተኮረ ነው። የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሺፈራው ሰለሞን እንደተናገሩት፤ አሁን ካሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ አራት ፓርኮችን ለመገንት የሚያስችል ጥናት እየተከናወነ ነው። አሶሳ፣ አረርቲ፣ አይሻና ሰመራ ከተሞች ላይ ለመገንባት እንደታቀደ ጠቁመው፤ በተለይ ሰመራ ላይ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት መሻሻልን ተከትሎ የወደብ አማራጭ በመኖሩ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል። አሶሳ ላይ ደግሞ የቀርከሃ ምርት በስፋት በመኖሩ ለቢሮ፣ ለቤት እቃዎችና መርከብ ግንባታ የሚሆን ግብዓት ለማምረት የሚያስችል የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት እየተጠና መሆኑን ጠቁመዋል። በቀርከሃ ምርት ለመሰማራት ቻይናዊያን ባለሃብቶች ከፍ ያለ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል። ''የጥናት ሂደቱ እንደተጠናቀቀ በውጤቱ መሰረት ወደ ግንባታ ይገባል'' ብለዋል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ መንግሥት ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ በትኩረት እየሰራበት ነው። እስካሁን በተለያዩ አከባቢዎች 12 ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን አስታውሰው ከተገነቡት ውስጥ ወደ ምርት የተሸጋገሩ አምስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የስራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ አወንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አመልክተዋል። ሀዋሳ፣ ቦሌ ለሚ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌና አዳማ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ከገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለፈው የበጀት ዓመት የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን አንስተዋል። እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፤ ፓርኮቹ ለ50 ሺህ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን 35 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በኮንትራት የሥራ እድል ተፈጥሯል። ይሁን እንጂ በአገሪቷ የታየው ሠላምና መረጋጋት እጦት፣ የሰራተኛ ፍልሰት ችግሮች ትልቅ ማነቆ እንደሆነ አብራርተዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ''ከዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ ከተፈለገ በተለይ መሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ በስፋት ሊሰራ ይገባል'' የሚል ሀሳብ አንስተዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ዩኒቨርሲቲዎች ስትራቴጂያዊ አጋርነት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም ነው ተወያዮቹ ያነሱት።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም