በዞኖቹ የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች ጨዋታ በዓል ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል እየተሰራ ነው

250

ባህር ዳር   ነሀሴ 3 / 2011 የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች ጨዋታ በዓል ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቆ በማክበር ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል እየሰሩ መሆናቸውን የሰሜን ወሎና ዋግ ህምራ ዞኖች ገለጹ።

በዓሉን የልጃገረዶች ጨዋታ በሚል በዓለም በማይዳሰሱ ቅርሶች ለማስመዝገብ የጥናት ወጤቶችና አስፈላጊ መረጃዎችን በማሟላት ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ የብርጓል አየለ እንዳሉት በዓሉ ከጥንት ጀምሮ ሴት ልጆች ነጻነታቸውን፣ አብሮነታቸውንና መተሳሰባቸውን የሚያጎለብቱበት ነው።

በዞኑ የሚከበረውን የአሸንድዬና ሶለል የልጃ ገረዶች በዓል ከነሐሴ 16 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ከጥንት ጀምሮ በነበረው የክዋኔ ሂዳት እንዲከበር ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዓሉ የሚከበርባቸው የላስታ ላል ይበላ፣ ቡግና፣ ግዳን፣ መቄትና ቆቦ አመራሮች በየቀኑ ከሌሎች ስራዎች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡንም አመልክተዋል።

በክልል ደረጃ ለሚከበረው ፌስቲቫልም 280 ልጃገረዶችን እንዲያሳትፉ ከክልሉ በተሰጣቸው ዕቅድ መሰረት ወረዳዎች ልጃገረዶችን እያዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመው፣ “በዓሉን በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይገባል” ብለዋል።

የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የባህልና ቱሪዝም ተወካይ አቶ ማሞ ታረቀኝ በበኩላቸው “ሻደይ የልጃገረዶች ፌስቲቫል የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ በዞን ደረጃ ትኩረት ተሰጥቷል” ብለዋል።

በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚገኙ ልጃ ገረዶች ከነሀሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በቡድን ሆነው ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ቁሳቁስ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።

በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም በበኩላቸው በዓሉ “የልጃገረዶች ጨዋታ” የማይዳሰሱ ቅርሶች በሚል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የጥናት ወጤቶችና አስፈላጊ መረጃዎች ተሟልተው ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች ፌስቲቫልን በክልል ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ ለማክበር አንድ አብይ ኮሚቴና አራት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው እየሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

እንደአቶ አለሙ ገለጻ በዓሉ በዋግና ሰሜን ወሎ ዞኖች ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርም በቢሮውና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዓሉ በዘመናት ብዛት እየተረሳና እየተዘነጋባቸው በመጡ ወረዳዎችም ጭምር በአሀኑ ወቅት እንደ አዲስ ለማክበር መነሳሳት መታየቱን ገልጸው፣ በክልል ደረጃ ለሚከበረው በዓል ዞኖች መላክ ያለባቸውን ተሳታፊ አስመልክቶ ዕቅድ መውረዱን ጠቁመዋል።

የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው የሁሉም ክልል የባህል አምባሳደሮች መጋበዛቸው መሆኑን የገለጹት አቶ መልካሙ፣ ይህም በዓሉን የአገር ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብና ለመስህብ ሃብት ለማዋል የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች በዓል ከነሀሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በባህር ዳር ከተማ በክልል ደረጃ እንደሚከበር ተመልክቷል ሲል የዘገው ኢዜአ ነው።