ድርጅቱ የተለያዩ የማምረቻ ኩባንያዎችን ያካተተ የኢንደስትሪ ማዕከል በ170 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ስራ ላይ አውሏል

73
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ  2/2011 የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የተለያዩ የማምረቻ ኩባንያዎችን ያካተተ የኢንደስትሪ ማዕከል በ170 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ። ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የማስፋፋት ስራዎች ያከናወነባቸውን ሰሚት ፓርትነስ፣ አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ፋብሪካ እና ዋንዛ ፈርኒሽንግ ኩባንያዎችን አስመርቋል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አረጋ ይርዳው እንደተናገሩት ለኩባንያዎቹ የማስፋፋት እና የማዘመን ስራ 286 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል። ከኩባንያዎቹ አንዱ የሆነው ‘ሰሚት ፓርትነስ’ የሪል ስቴት ኩባንያ ከሌሎች ሪል ስቴት አልሚዎች ለየት ባለ መልኩ በማምረቻ ኢንደስትሪ ላይ ያተኮረ ማዕከል ገንብቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል። ለማዕከሉ ግንባታም 170 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉንና ግንባታው፣ የአትክልት ቦታዎችንና ለሰራተኞች ደህንነት የተሟላ ሁኔታዎችን ያካተተ መሆኑንም አክለዋል። በአሁኑ ወቅትም በማዕከሉ የተለያዩ ኩባንያዎች ተሰማርተው እንደሚገኙና በቀጣይም ሌሎች ፋብሪካዎች፣ ቢሮዎች፣ የህክምና ማዕከላትና የህጻናት ማቆያዎችን ለመገንባት በሂደት ላይ ነው ብለዋል። እንደ ዶክተር አረጋ ገለጻ በዋንዛ ፈርኒሽንግ እና አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ፋብሪካዎችም ዘመኑ የሚጠይቃቸውን ቴክኖሎጂዎች በማሟላት የምርቶች አይነትና ምርታማነት የማሻሻል ስራ ተሰርቷል። ኩባንያዎቹ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ አገራት የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ለማዳንም የጎላ ሚና እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል። የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ተካ ገብረእየሱስ በበኩላቸው የኢንደስትሪ ማዕከሉ ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚከናወኑ ስራዎችን ለመደገፍ የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ ከመንግስት ወደ ግል ይዞታ የተዘዋወሩ ኩባንያዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዘ  አመርቂ  እንቅስቃሴ እንዲያከናውኑ እያስቻለ መሆኑንም አንስተዋል። የኩባንያዎቹ መስፋፋት የውጭ ምንዛሬን  በመቀነስ፣ በስራ እድል ፈጠራና ለሌሎች አምራች ኢንደስትሪዎች ግብዓት በማቅረብ በኩልም የሚኖራቸውን ጠቀሜታዎች ጠቅሰዋል። ድርጅቱ እያከናወነ ያለው ስራ ለሌሎች የግል ኩባንያዎችም አርአያ የሚሆንና የግሉን ዘርፍ በማምረቻው ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያበረታታ ነው ሲሉም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም