በአዲስ አበባ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና የምክክር መድረክ ሊካሄድ ነው

200

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ  2/2011 የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና የምክክር መድረክ ነሐሴ 8 እና 9 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል።

“ፊን ቴክ” የሚል ስያሜ ያለው አውደ ርዕይና የምክክር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱንና የፋልኮን ኢንዱስትሪያል ማርኬቲንግ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አውደ ርዕይና የምክክር መድረኩን በጋራ ማዘጋጀታቸው ተገልጿል።

የፋልኮን ኢንዱስትሪያል ማርኬቲንግ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮናታን ሙሉ ለኢዜአ እንደገለጹት የአውደ ርዕዩና የምክክር መድረኩ አላማ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉ ስራዎች በቴክኖሎጂ እንዲከናወኑ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የዘርፉ ተዋናዮች እንዲገናኙ መድረክ መፍጠር ነው።

የፋይናንስ ተቋማት እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአንድ መድረክ በማገናኘት እርስ በእርሳቸው በመወያየት የቢዝነስ ትስስር እንዲፈጥሩ ለማድረግም አውደ ርዕዩና የምክክር መድረኩ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ባንኮች፣ማይክሮ ፋይናንሶችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎታቸውን ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበትና ለዚህም አውደ ርዕዩና የምክክር መድረኩ መዘጋጀት ተቋማቱ ያሉትን የቴክኖሎጂ አማራጮች ለመመልከት ያስችላቸዋል ብለዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆንና በፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል ያለው ዝግጁነት ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑ የፋይናንስ ቴክኖሎጂው ፈተናዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፋይናንስ አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ ለሚሰጡ ተቋማት እያደረገ ድጋፍና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዘርፉ ገና ያልተነካ ገበያ መሆኑ በዘርፉ መልካም የሚባሉ አጋጣሚዎች እንደሆኑም ነው አቶ ዮናታን ያስረዱት።

የአውሮፓና የእስያ አገራት በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑንና ካለት የገበያ እድል አንጻር ኢትዮጵያም የዚሁ ተጠቃሚ የመሆን አጋጣሚዋ ሰፊ እንደሆነም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ከ10 እስከ 15 ዓመት ባለው ጊዜ የፋይናንስ ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂው እንደሚጠቀለልና ለዚህም መልካም የሚባሉ አጋጣሚዎች እየሰፉ መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ላይ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ያተኮረ የፓናል ውይይት ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚካሄድና በውይይቱ ላይ ከ50 በላይ ድርጅቶች እንደሚሳተፉም ጠቅሰዋል።

የቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች የሆኑ ስድስት የግል ፋይናንስ ድርጅቶች በአውደ ርዕዩ የሚሰጡትን አገልግሎት ለተሳታፊዎች እንደሚያሳዩም ገልጸዋል።

አውድ ርዕዩን ከ300 በላይ ተሳታፊዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል።

የፋልኮን ኢንዱስትሪያል ማርኬቲንግ በቀጣይ በሚካሄዱ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና የምክክር መድረኮች የውጭ ተቋማት ለማሳተፍ እቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በቀጣዩ ሳምንት ከሚካሄደው የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና የምክክር ተሞክሮ በመውሰድ በቀጣይ በውጭ አገራት መሰል ኩነቶችን ለማዘጋጀት ድርጅቱ እቅድ አለው ብለዋል።