የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የሚመራበት ረቂቅ ህግ እየተዘጋጀ ነው

251

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሐሴ  2/2011 የትምህርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የሚመራበት የመጀመሪያ የሆነው “የትምህርት ህግ” ረቂቅ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፍኖተ ካርታ አማካሪ አቶ ከፍያለው አያኖ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እስካሁን የትምህርት ስርአቷ የሚመራበት ህግ አልነበራትም።

በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ለሚፈጸም የወንጀልም ሆነ የፍትሐ ብሔር ጥፋትን ህጋዊ ስርዓት ማስያዝ የሚቻልበት አሰራር እስካሁን አልነበረም።

“አንድ ተማሪ ብሄራዊ ፈተና ሲኮርጂ ቢያዝ በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት የአሰራር ስርዓት ወይም ህግ የለም” ያሉት አቶ ከፍያለው አሁን ግን ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው።

ረቂቁ የህግ ማዕቀፍ ትምህርት ነክ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ መሆኑም ታውቋል።

የተማሪ ወላጆች ፣ የግል ተማቋት ተማሪዎችና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትምህርት የሚመለከታቸው አካላት በትምህርት ህጉ ረቂቅ ሰነድ ዝግጅት ላይ ተካተዋል ብለዋል።

በአንድ ተማሪ ላይ አላስፈላጊ የቅጣት አርምጃ ቢወሰድበት ወይም የአካል ጉዳት ቢደርስበት በሚዘጋጀው የትምህርት ህግ ውሳኔ ያገኛል ብለዋል።

የረቂቅ ሰነዱ ዝግጅት የተጠናቀቀ መሆኑን የገለጹት አቶ ከፍያለው ፤ በቀጣይ ህዝባዊ ውይይት ተደርጎበት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ ይቀርባልም ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣ ኮሌጆችና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተማሪዎች የማፍራት ውስንነት እንዳለባቸው ይነገራል።