የኃይማኖት ተቋማት ፍትሓዊነትን፣ አሳታፊነትንና አኩልነትን መሰረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት ፍትሓዊነትን፣ አሳታፊነትንና አኩልነትን መሰረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል
ነሐሴ 2 / 2011 የኃይማኖት ተቋማት ፍትሓዊነትን፣ አሳታፊነትንና አኩልነትን መሰረት አድርገው በመስራት ትክክለኛውን አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኃይማኖት ተቋማት መልካም አስተዳደር ችግሮች ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት እያካሄደ ይገኛል። ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው ውይይት ''መልካም አስተዳደርና ኢስላማዊ አስተምህሮ'' በሚል ርዕስ ጥናታዊ ዕሁፍ ቀርቧል። ጽሁፉን ያቀረቡት ዶክተር ኢድሪስ መሓመድ እንደሚሉት በዚህ ወቅት ትልቁ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ "ትውልዱ በስነ ምግባር አለመታነጹ ነው" ይላሉ። በተለይም የኃይማኖት አባቶች በሁሉም ዘርፍ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለመቻላቸው አሁን ለሚታየው ዘርፈ ብዙ ችግር ዳርጎናልም ብለዋል። በእስለምና ዕምነት ብቻ ቢታይ ከከፍተኛው ኢስላማዊ መዋቅር እስከ ታችኛው መስጊድ ድረስ ያሉ የእምነት መሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። የጎሮ ሓምዲያ መስጊድ ኢማም ሼህ ሁሴን አወልም እንዲሁ ከዚህ በፊት በእስልምና ኃይማኖት ውስጥ ተከስቶ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር ምዕመኑን መጠራጠር ውስጥ ከቶ ነበር ብለዋል። በመሆኑም የኃይማኖት መሪዎች ተክክለኛውን የፈጣሪ መንገድ በመያዝ ተከታዮቻቸውን ማስተማርና መምራት አለባቸው ብለዋል። ከምንም በላይ አሁን በትውልዱ በስፋት የሚስተዋለውን የግብረ ገብነት ችግር ለመፍታትም የኃይማኖት መሪዎች ዘላቂ ሰላም ላይ አተኩረው ሊሰብኩ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ሌላው የሆሎፋ ረሺድ መስጊድ ኢማም ሼህ መሓሙድ ጁሓር መሓመድም የኃይማኖት ተቋሙ ውስጥ "ሰፊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይስተወላል" ይላሉ። እሳቸው እንደሚሉት እስካሁንም ድረስ ያልተፈቱና ከላይኛው አርከን እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ምዕመኑን ለተለያዩ ብሶቶች እያዳረጉ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ ነው ያሉት። ችግሩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም ጉዳቱ የከፋ ስለሚሆን የኃይማኖት መሪዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መፍትሔ ሊያበጁለት እንደሚገባ አሳስበዋል። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምከር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን በበኩላቸው ችግሩ የኃይማኖት ተቋማትን ብቻ ሳይሆን አገርንም የሚጎዳ በመሆኑ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል። በተላይ ደግሞ የኃይማኖት መሪዎች ኃላፊነትና የአስተዳደር ስራ ከፈጣሪ የተሰጣቸው አደራ መሆኑን አውቀው የተሰጣቸውን አደራ በትክክል ሊፈጽሙ እንደሚገባ አሳስበዋል። በሰላም ሚኒስቴር የእምነትና የኃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ጌተዋ ደስታው እንደሚሉት መንግስት ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ የኃይማኖት ተቋማት ችግራቸውን እንዲፈቱ እያገዘ ይገኛል። ዳይሬክተር ጄነራሉ በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ በሰልጣን ምክንያት ሽኩቻዎች፣ የሃብት አስተዳደር ችግሮችና የሰው ኃይል አያያዝ ችግሮች በስፋት ይታያሉም ብለዋል። እነዚህ ችግሮች በጊዜ ካልተፈቱም ቀውስ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ መንግስት ችግሩ እንዳይባባስ ለማድረግ ነጻነታቸውን በጠበቀ መልኩ እየደገፈ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በውይይቱ እስካሁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ መካነ እየሱስና የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያናት የተሳተፉ ሲሆን ውይይቱ ነገም ይቀጥላል ተብሏል።