በጋምቤላ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ያደረሰ የፖሊስ አባል ተያዘ

75
ነሀሴ 1/2011   በጋምቤላ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸመ የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቶው ኡኮት ጥቃቱን አስመልክቶ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት አባሉ ጉዳቱን ያደረሰው ከተመደበበት ቦታ በመልቀቅ መናኸሪያ አካባቢ ሄዶ ተኩስ በመክፈት ነው። ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ በደረሰው ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድርሱም ተገልጿል። ይሔን ተከትሎ ከተፈጠረው ግርግር ጋር ተያይዞም ሌሎች አራት ሰዎች በድንጋይ ውርወራ ጉዳት ሲደርስባቸው የፖሊስ አባሉ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች በጋምቤላ ሆስፒታል አስፈላጊው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው በወቅቱ በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ግርግርም በፀጥታ አካላት ጥረት ወደ ነበረበት መረጋጋት መመለሱን አስታውቀዋል። በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን የገለጹት ኃላፊዎቹ ጉዳዩ የአንድ ግለሰብ መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ በተረጋጋ መልኩ የተለመደውን የዕለት ተዕለት ተግባሩን ያለስጋት ማከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል። በተጨማሪም ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የጠየቁት ኃላፊዎቹ በጥቃቱ ያለፈ የሰው ህይወት እንደሌለም አመልክተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም