በክልሉ የመኸር እርሻ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ተሸፍኗል

81
አዲስ አበባ  ነሀሴ 1/2011 በኦሮሚያ በ2010/11 የምርት ዘመን እስካሁን ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። ክልሉ በምርት ዘመኑ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ምርቶች ለመሸፈን ነው ያቀደው። እስካሁን ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የተሸፈነ ሲሆን 180 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ለኢዜአ ገልጸዋል።በምርት ዘመኑ ምርታማነትን በሄክታር ወደ 29 ኩንታል ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል። ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ከ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም በቂ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉን ጠቅሰዋል። የምርት ግብዓቶች በዩኒየኖች አማካይነት ሲጓጓዙ ካጋጠመ ክፍተት በቀር የአቅርቦት ችግር እንደሌለም አክለዋል። ችግሩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት መፍታት እንደተቻለም ነው አቶ እንዳልካቸው የገለጹት። በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር በቂ ዘር ባለመዘጋጀቱ የበቆሎ ዘር እጥረት አጋጥሞ የነበረ ቢሆንም በሌሎች ተተኪ ሰብሎች መሸፈኑን ተናግረዋል። በመኸሩ በቂ ዝናብ የነበረ መሆኑና አርሶ አደሩም በከፍተኛ ተነሳሽነት ስራው ላይ መሰማራቱ 'የታቀደውን ለማሳካት ያስችላል' ብለዋል። ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ጥቁር አፈርን በቢ.ቢ.ኤም ማረሻ ማረስ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም፣ አሲዳማ መሬትን በኖራ ማከምና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በስራ ላይ መዋላቸውንም ጠቅሰዋል። በክልሉ የኤጀርሳ ለፎና የደንዲ ወረዳዎች አርሶ አደሮች በበኩላቸው በዚህ ዓመት የዝናቡ ሁኔታ ጥሩ በመሆኑ አመርቂ ምርት ማግኘት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። የምርት ግብዓቶች በወቅቱ ሰለቀረቡላቸው በጥሩ ሁኔታ መዝራታቸውንና ቡቃያው ያለበት ሁኔታም መልካም መሆኑን ገልጸዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም