ስልጠናው የመንግሥት ኃላፊነትንና የህዝብን አደራ የሚፈጽሙበት አቅም ይፈጥርልናል--የምሥራቅ ወለጋ አመራሮች

47
ነቀምቴ ነሐሴ 1 / 2011 በምስራቅ ወለጋ ዞን ለአመራሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና የመንግሥት ኃላፊነትንና የህዝብን አደራ የሚፈጽሙበት አቅም እንደሚፈጥርላቸው ሰልጣኞች ገለጹ። ከሰልጣኞቹ አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንዳስረዱት የማስፈጸም አቅም በዞኑ እየተካሄደ ያለው ስልጠና ኃላፊነታቸውን ለመወጣትና ህዝብን ለማገልገል ያስችላቸዋል። ከነዚሁ የቀበሌ አመራሮች መካከል የጉቶ ጊዳ ወረዳ የሜጢ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ አምሣሉ ገመቹ በሥልጠናው የሚያገኙት ግንዛቤ ሕዝቡን በተሻለ መንገድ ለማገልገል እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ፡፡ ሥልጠናው በየቀበሌው የሚታዩትን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት ለሕዝቡ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት ያስችለኛል ብለዋል፡፡ ሥልጠናው የተጣለባቸውን የሕዝብና የመንግሥት አደራ ለመወጣትና ለውጡን በማስቀጠል የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት እንደሚያስችላቸው የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ወረዳ የሎኮ ቀበሌ የሴቶች ፣ህፃናትና ፣ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ ለሜሣ ናቸው፡፡ የዋዩ ቱቃ ወረዳ የሐሮ ጫልቺስ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ካሣሁን ወዳጆ በበኩላቸው በሥልጠናው የማስፈጸም አቅምን እንደገነባላቸውና ዕውቀታቸውን ከዕለት ሥራቸው ጋር በማዋሃድ ለመልካም አስተዳደርና ለአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ፈጣንና ቀልጣፋ መልስ ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አቅምና የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ለማሳደግ እንደሚያበቃቸው ገልጸዋል ፡፡ ወይዘሮ ዓለሜ ጪብሣ በበኩላቸው በመልካም አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታትና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሥልጠናው አስፈላጊ ነው ይላሉ ፡፡ ከሥልጠናው በኋላ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያስችለኛል ብዬ አምናለሁ ብለዋል ፡፡ ስልጠናው የኦሮሞ ሕዝብ የብሔር/ብሐረሰቦችን መብትና እኩልነት በማክበርና በማስከበር፣በመፈቃቀር፣በመቻቻልና በመረዳዳት የሚኖሩባት አገር ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ በዞኑ 17 ወረዳዎች ለሚገኙ 337 ቀበሌዎች ከ2ሺህ696 የቀበሌ አመራሮች ሥልጠና በመሰጠት ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም