በዱብቲ ሆስፒታል ነጻ የዓይን ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

83
ሰመራ ሚያዝያ 26/2010 የአፋር ክልል ጤና ቢሮ "አልበሰር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን" ከተባለ የፓኪስታን የሕክምና ቡድን ጋር በመተባባር ለሕብረተሰቡ ነጻ ዓይን ሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀመረ። የሕክምና ቡድኑ አገልግሎቱን ትናንት በዱብቲ ሆስፒታል መስጠት የጀመረ ሲሆን በስድስት ቀናት ቆይታውም ከ8 እስከ 10 ሺህ ለሚደርሱ ሰዎች የአይን ሞራ ገፈፋና ተያያዥ የዓይን ሕክምናዎችን እንደሚሰጥ ሆስፒታሉ አስታውቋል። ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች የነጻ ሕክምናው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረቡት ዶክተር ሀሰን፣ አገልግሎቱም ሕሙማን ለመሰል ህክምና ወደ ደሴ፣ መቀሌና አዲስ አበባ በመሄድ ይደርስባቸው የነበረውን እንግለትና ወጪ እንደሚታደግ ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የሆስፒታሉ የዓይን ኃኪሞች ጠቃሚ ልምድና እውቀት ለማግኘት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አመልክተዋል። የአልበሰር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሺን የዓይን ሕክምና ቡድን መሪ ሚስተር ፈክሩዲን ዳካን እንደተናገሩት ድርጅቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2000ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል። በአፋር ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ትናንት በዱብቲ ሆስፒታል በተጀመረው ነጻ የሕክምና አገልግሎትም የዓይን ሞራ ገፈፋን ጨምሮ የምርመራ፣ የመነጽር፣ የመድኃኒትና ተያያዥ አገልግሎቶችን ለመስጠትና በእዚህም ከ8 እስከ 10ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታሰበቡን ገልጸዋል። ሕክምና ለማግኘት ከሚሌ ወረዳ ወደዱብቲ ሆስፒታል የመጡት ወይዘሮ ሀሊማ ሙሳ እንደተናገሩት አንድ ዓይናቸው በዓይን ሞራ ተሸፍኖ በተለይ ማታ ማታ በቀላሉ ለመንቀሳቀስ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል። ይሁንና በሆስፒታሉ በነጻ የተሰጣቸው የዓይን ሞራ ገፈፋ ሕክምና የዓይናቸው ጤና እንደሚሻሻልና የተሰማሩበትን የግል ሥራ በአግባቡ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ከአይሳኢታ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ እታፈራሁ አበበ በበኩላቸው የዓይን ሕመም የጀመራቸው ከአምስት ዓመት በፊት እንደሆነና በቅርቡ እየባሰባቸው መምጣቱን ተናግረዋል። ወደ መቀሌ ከተማ በመሄድ ለመታከም ቢሞክሩም ለሕክምና አገልግሎቱ ረጅም ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ወደ መቀሌ ከተማ ለሕክምና ተመልሰው ለመሄድ የገንዘብ ችግር ስለገጠማቸው ተስፋ ቆርጠው እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ እታፈራው፣ በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ነጻ የምርመራና የሕክምና አገልግሎት የዓይን መነጽር በማግኘታቸው ተስፋቸው መለምለሙን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም