የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያና አፍሪካ ሕብረት ምስጋና አቀረበ

145
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሐሴ 1/2011በ  የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላማዊ ሽግግር እንዲደረግ ለተጫወቱት ሚና የምስጋና ፕሮግራም አዘጋጅቷል። በሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤትና በለውጥ አራማጅ ሃይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር የሽግግር ሕገ መንግስትና የፓለቲካ ስምምነት በመፈራረም መጠናቀቁ ይታወሳል። ኢትዮጵያና አፍሪካ ሕብረት ሁለቱን ወገኖች በማደራደር ላበረከቱት አስተዋጽኦና ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት የምስጋና ፕሮግራም አካሂዷል። በምስጋና ፕሮግራሙ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ዳይሬክተር ጄኔራሎች በተገኙበት ሽልማት አበርክቷል። ሽልማቱ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሱዳን ልዩ ልዑክ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፣ በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶና የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዑክ መሃመድ ሃሳንላባት መሰጠቱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ያደረሰን መግለጫ ያሳያል። የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት የፖለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ ጄኔራል ሸምሰዲን አልካባሺ በተገኙበት የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦስማን ዳሃብ ሽልማቱን አበርክተውላቸዋል። አምባሳደር ኦስማን ዳሃብ በሽልማት ስነ ስርአቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን እና የሽግግር መንግስት ለመመስረት ሲካሄድ በቆየው የድርድር ሂደት በአደራዳሪነት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ድርጊቱ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑንም ገልጸዋል። የምስጋና ፕሮግራሙ በሁለቱ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርና በተለያዩ የትብብር መስኮች ለሚከናውኑ ተግባራት ጥረት መልካም መደላድል ይሆናል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም