የመንገድ ያለህ

67
ሰለሞን ተሰራ: ማልዶ ወደ ስራ የሚሮጠው ባተሌ በጠቅላላ የኑሮ ውጣ ውረድ ያስቆዘመው፣ የእለት እንጀራ የሚያሳስበው፣ ስራ አረፈድኩ ብሎ የሚዋከብ፣ ልጄን ትምህርት ቤት አድርሼ ውሎዬን እጀምራለሁ የሚል ነው። አለፍ ሲልም መንገደኛው ወደተለያየ ማህበራዊ የህይወት መስመሩ ሊተም ይችላል። በዚህ ሁሉ ውክቢያ ውስጥ የአዲስ አበባ መንገዶች በጎዳና ነጋዴዎች ተጣበው፣ በንግድ ቤት ድንኳን ተከልለው፣ በማን አለብኝ ባለሃብት ድንጋይና ጠጠር ተዘግተው በመንገድ ዳር ጋራዥ ተጨማልቀው ሸቀጣቸውን የእግረኛ መንገድ ላይ ባከማቹ ሱቆች ማን ይነካኛል ትዕቢት እግረኛውን ወደ መሃል በመንዳት ከመኪና ጋር ያጋፉታል። የከተማችን ሞተረኞች፣ ሚጢጢ ባጃጆች፣ ጤና የራቃቸው የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎችና ባደረሱትና በሚያደርሱት አደጋ የተነሳ 'ቀይ-ሽብር' የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው ሲኖትራኮች ደግሞ እግረኛውን ተቀብለው በጥሩንባቸው እያስደነበሩ አቅሉን ያስቱታል። በአዲስ አበባ ለእግረኞች በተሰሩ መንገዶች ላይ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ድርጊቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን ከላይ ያነሳናቸው ጉዳዮች ቁልጭ አድርገው ያሳብቃሉ። በፊት በፊት የእግረኛ መንገድን የሚዘጉት በማን አለብኝነትና በእብሪት አሸዋ፣ ድንጋይና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶችን በሚደፉ ባለሃብቶች እና መንገድ ዘግተው የካፌ ጥላ በሚዘረጉ ነጋዴዎች ብቻ ይዘጋ የነበረው የእግረኛ መንገድ አሁን አሁን የሚዘጋውና የሚያደናቅፈው እየበዛ መጥቷል። በሳይንሳዊ ጥናት አንድ መንገድ የሚገነባው የእግረኛ መንገድን ታሳቢ አድርጎ ሲሆን ሰባት ሜትር ስፋት ያለው መንገድ ሲገነባ አንድ ነጥብ አምስት ሜትሩ ለእግረኛ ይተዋል። 20 ሜትር ስፋት ባለው መንገድ ደግሞ ግራና ቀኝ ሶስት ሶስት ሜትር የእግረኛ መንገድ እንዲኖረው ይደረጋል። ባለ 50 ሜትር ስፋት ያላቸው ዋና ዋና መንገዶች ደግሞ በግራና በቀኝ አምስት አምስት 10 ሜትሩ ለእግረኛ የሚተው ነው። ልኬቱን ለባለሙያው እንተወውና ለእግረኛ ተብለው የሚሰሩ መንገዶች የእግረኛነታቸው ቀርቶ ለተለያየ አገልግሎት እየዋሉ ነው። መንገደኛውም መንገዱን በመነጠቁ ትቶ በመውጣት ለተሽከርካሪ በተፈቀደ መንገድ በመሄድ ለአደጋ ተጋላጭነቱ እያደገ መጥቷል። የእግረኛ መንገዶች ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ ለተለያዩ ህገወጥ ተግባራት መከወኛ እየዋሉ መሆኑን ለከተማዋ ነዋሪ መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው። ከችግሩ ጋር መኖር ከጀመረ ውሎ ማደር አይደለም ሰንበትበት ብሏል። በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የህገወጥ ንግድ ግብይትን መመልከት እንግዳ ነገር አ ይደለም። በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት በመዲናዋ ዋና ዋና የሚባሉ አካባቢዎች ይሄው የመንገድ ዳር ግብይትና ግርግር ከተዋሃዳቸው ቆይቷል። ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው አትክልት፣ አልባሳት፣ የቤት እቃዎች፣ ሌላም በአስፋልት መንገድ ዳር የሚሸጡ ጥቂቶች አይደሉም። ለእግረኞቹ ችግር የሆኑት እነዚህ ነጋዴዎች ህጋዊ ባልሆነው ግብይት ምክንያት በደንብ አስከባሪ እና ፖሊስ መሳደዳቸውም የዕለት ተዕለት ትዕይንት ነው። ነጋዴዎቹ ደንብ አስከባሪዎች ሲመጡባቸው ለማምለጥ በሚያደርጉት ሩጫ ለመኪና አደጋ እንደሚጋለጡ እሙን ነው ። ነገር ግን የዚህ ችግር ምክንያት ዘርፈ ብዙ መሆኑን የሚናገሩት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል “ በእግረኛ መንገድ ላይ ህገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙት ግለሰቦች ብቻ አይደሉም።” “የመንግስት ተቋሞች ለምሳሌ ዘላቂ ልማትና መናፈሻ በከተማ ውበት ላይ የሚሰራ ኤጀንሲ አትክልት ጉድጓድ ለመትከል የሚቆፍርበት ሁኔታ አለ። በተለይ በአስፋልት መሃል ላይ አፈር የሚደፉበት ሁኔታ አለ። ቀይ አፈር በሚደፉበት ጊዜ አፈሩ ወደ አስፓልት ይመጣና ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ አስፓልቱ በሙሉ ጭቃ የሚሆንበትን ጊዜ ብዙ ነው።”ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ባለስልጣኑ በትኩረት የሚሰራው በመንገድ ግንባታ ላይ እንጂ የመንገድ ደህንነት ማስከበር ላይ እንዳልነበር አቶ ጡዑማይ አስታውሰዋል። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በከተማዋ አምስት የመንገድ አስተዳደር ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ከፍቶ ከግንቦት 2009 ጀምሮ ወደ ስራ መግባቱን መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በእግረኛ መንገድ ላይ የተለያዩ ህገወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦችና ድርጅቶችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ተግባር መጀመሩንም ሃላፊው በወቅቱ ቢናገሩም አሁንም የተለወጠ ነገር አለመኖሩን ዘወትር ስናልፍ ስናገድም እየታዘብን ነው። ባለስልጣኑ በ2011 በጀት ዓመት መንገድ ማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ቢገልጹም የተያዘው በጀት አመት ማጠናቂያ ላይ ደርሰንም በመንገድ ማጣት መከራችንን እያየን የመንገድ ያለህ እያልን ነው። ለአብነትም ባለስልጣኑ ቀደም ሲል ህንጻ ለሚገነቡ ግለሰቦች መንገድ ላይ ለግብዓት ማስቀመጫ በሚል ፈቃድ ይሰጥ እንደነበርና ይህ አሰራር አግባብ ባለመሆኑ ህንጻ አሰሪው በራሱ ይዞታ ላይ እንዲያስቀምጥ ታስቦ ፈቃድ መስጠት መከልከሉን ከአመት በፊት ቢናገሩንም አሁንም ባለሃብቶቹን ሃይ የሚል መጥፋቱን ከተማዋን ዞር ዞር ብሎ በመታዘብ ማረጋገጥ ይቻላል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የተዘጋጀውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖረት መሠረት በማድረግ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው ግብረ መልስ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በመንገድ ደህንነት ዙሪያ በተገቢው መጠን ባለመሥራቱ አገሪቱን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጋት መሆኑ ተናግሯል፡፡ ማንኛውም አካል በተሽከርካሪ ወይም በእግረኞች መንገድ እንቅስቃሴዎችን በሚያውክ መልኩ ቁሳቁስ ወይም ሸቀጥ እንዳያስቀምጥ፣ እንዳይነግድ፣ እንዳያበላሽና እንዳይቆፈር ከቆፈረ በኋላም እንዲደፍን የወጣውን ደንብ ተፈፃሚነቱን እንደማይከታተሉ በኦዲት ግኝቱ መረጋገጡንም ይፋ አድርጓል፡፡ የአስተዳደሩ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ በእግረኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የአሥር ዓመት ስትራቴጂ በማውጣት ከፍተኛ የእግረኛ እንቅስቃሴዎች ባሉባቸው እንደ መገናኛ፣ መርካቶ ፣ ፒያሳና ቸርችል ጎዳና ባሉ ሥፍራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛ መንገዶች፣ የእግረኛ ማቋረጫዎችና የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችም ይለማሉ በማለት ባለፈው ሚያዚያ አስታውቋል፡፡ ግን እነዚህ መንገዶች ከተገነቡ በኋላ የሚቆጣጠራቸውና የሚንከባከባቸው አካል ህገ ወጦች እንዳያበላሿቸው የራሱን እርምጃ ካልወሰደ እኛም ወደ መሃል አስፋልት መገፋታችን አይቋርጥም መንገዶቹም የሰው ያለህ እያሉ መጓዛቸው አያበቃም።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም