በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል የተካሄደው ውይይት “ጠንካራ መግባባትና መተማመን የተፈጠረበት ነው” – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

3926

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ መካከል የተካሄደው የሁለትዮሽ ውይይት “የቆዩ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችልና ጠንካራ መተማመን የተፈጠረበት ነው” ሲሉ በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሚመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በግብጽ ለሁለት ቀናት የተሳካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርጓል።

አገሮቹ ለዘመናት የቆየ የታሪክ፣ የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው፣ በመሪ ደረጃ በየወቅቱ እየተቀራረቡ በመወያየት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በመስራት ላይ የሚገኙ ናቸው።

ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በመጋቢት 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በያዝነው ዓመት ጥር ላይ ግብጽን በመጎብኘት በሁለትዮሽ፣ በአህጉርና በዓለምአቀፍ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ከትናንት በስቲያ በፕሬዚዳንት አል ሲሲ በግብጽ ብሄራዊ ቤተ መንግስት ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም በቆይታቸው ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

በተለይም አገሮቹ ግብርናን፣ የዓሳ ኃብት ልማትንና መሰረተ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙትን ግብጻውያን ባለኃብቶች ቁጥር ለማሳደግና በኢትዮጵያ የግብጽ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባት ለአገሪቷ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርም  አገሮቹ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

መሪዎቹ በውይይታቸው በግብጽ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ለማፋጠን የሚያግዝ ፈንድ ማቋቋም በሚቻልበት መንገድ ላይም ትኩረት ሰጥተው ተወያይተዋል።

የመሪዎቹን ውይይት የተከታተሉት በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለጋዜጠኞች እንዳሉት “በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት ከዚህ በፊት የነበረውን ሁለንተናዊና መልካም ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ያስቻለ ነው።”

ኢትዮጵያና ግብፅ ያላቸው ትስስር በአባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ ምክንያት የተሳሰረ በመሆኑ ይህን ግንኙነታቸውን በመተማመን ላይ በተመሰረተ መንገድ ለመገንባት ጥረት እንደሚያደርጉም መሪዎቹ ማረጋገጣቸውን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ፕሬዚዳንት አል ሲሲ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ግብጽ የኢትዮጵያን ፍላጎት፣ ደህንነትና መረጋጋት መሰረት ያደረገ ስትራቴጂያዊ ግንኙነቷን ታጠናክራለች።

በኢትዮጵያ የፌደራል የስራ ቋንቋ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበኩላቸው “እኛ ኢትዮጵያዊያን ወንድምነትና ጉርብትናን የምናውቅ፤ እግዚአብሄርን የምንፈራ ስለሆንን፤ ወንድም ህዝብ የሆነውን የግብጽ ህዝብ በፍጹም፣ በፍጹም የመጉዳት ሃሳብም ፍላጎትም የለንም” በማለት ዳግም ለግብጽ መንግስትና ህዝብ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

መሪዎቹ በውይይታቸው መጨረሻ ላይ እንዳረጋገጡት፤ ሁለቱ አገሮች እርስ በርስ ከመጠራጠር ወጥተው አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በመተባበር ሰርተው በቀጣናው አርዓያ የሚሆን ግንኙነት የመመስረት ፍላጎት አላቸው።

“መተባበር ብዙ ትሩፋት አለው፤ በመቀናጀት እድገት ይመጣል፣ አለመስማማት ዋጋው ኪሳራ ነው፤ ተፈቃቅደን ተስማምተን መስራት እንችላለን” የሚሉ ሀሳቦች በውይይቱ ወቅት መንጸባረቃቸውን ነው አምባሳደር ታዬ የገለጹት።

አምባሳደር ታዬ እንደሚሉት፤ ውይይቱ ከዚህ ቀደም የነበሩ አለመግባባቶች በወሳኝነት መፍታት የሚያስችል መግባባትና ጠንካራ መተማመ የተፈጠረበት ነው።

“ምንም እንኳን ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የመሪዎቹ ውይይት በመጠራጠር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሽሮ ለሁለቱ አገሮች ህዝቦች የጋራ ጥቅም ለመስራት የተግባቡበት ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምታካሂደው ለልማት ብቻ መሆኑን ግብጽም እውቅና የሰጠችበት መድረክ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም ከ65 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ብርሃን ማግኘት እየናፈቀው አባይ ሳይለማ መቅረት እንደማይቻል፣ ለግብጻዊያንም አባይ ምን ማለት እንደሆነ በመገንዘብ ግድቡን በመገንባት ጉልህ ተጽእኖ ለመፍጠር እንደማይሞከር በግልጽ ውይይት እንደተደረገበት ገልጸዋል።

“በመሪዎቹ ውይይት የግድቡ መገንባት ጉልህ ተጽእኖ ሊያመጣ እንደማይችል፤ ኢትዮጵያም ይህን ለማድረግ ፍላጎቱም አቅጣጫውም እንደሌላት አጽንኦት ተሰጥቶታል ማለት ይቻላል” ብለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው “የውይይቱ መንፈስ እጅግ ፍሪያማ በጣም ገንቢ የሚባል፤ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሸጋግር የሚችልና ጥሩ ውይይት ነው” በማለት ገልፀዋል።

ውይይቱ የተካሄደው ከአባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ በግብጽ ህዝብ ዘንድ ያለውን ስጋት ለመቀነስና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ መካሄዱንም አቶ ካሳሁን ገልጸዋል።

በፕሬዚዳንት አል ሲሲና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት በግብጽ እስር ቤት የቆዩ 32 ኢትዮጵያዊያን እስረኞችንና በትጥቅ ትግል ሲሳተፉ የቆዩ የኦነግ አመራሮችን ወደ አገራቸው ይዘው ተመልሰዋል።

ከሁለት ወራት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ግብጽን ጨምሮ በኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የስራ ጉብኝት አድርገዋል።