የተጓደሉ የስራ ሃላፊዎችን ለማሟላት የሚመለከታቸው አካላት የተሻሉትን እንዲጠቁሙ ተጠየቀ

65
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና እምባ ጠባቂ ተቋም የተጓደሉ የስራ ሃላፊዎችን ለሟሟላት የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት ለዘርፉ የሚመጥኑ እጩ እንዲጠቁሙ የሁለቱ ተቋማት እጩ አቅራቢ ኮሚቴዎች ጠየቁ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የእምባ ጠባቂ ተቋም እጩ አቅራቢ ኮሚቴዎች ዛሬ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ እና በሶስት የቅርንጫፍ እምባ ጠባቂዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት የህፃናትና ሴቶች ኮሚሽነር እጩዎችን ከሰኔ 1 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በስልክ፣ በኢ-ሜይልና በፋክስ መጠቆም ይቻላል ተብሏል። የህዝብ እምባ ተባቂ ተቋም የእጩ አቅራቢ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ሀለፎም ግደይ እንዳሉት፤ ተቋሙ ዋና እምባ ጠባቂ እንዲሁም በሰመራ፣ ጋምቤላና አሶሳ የቅርንጫፍ እምባ ጠባቂዎች የሉትም። በመሆኑም በነዚህ ያልተሟሉ ክፍት ቦታዎች ህገ መንግስቱን የሚያስከብሩ፣ አስፈፃሚ አካላት የሚያደርሱትን በደል በመከላከል ለህገ መንግስቱ ተገዥና ለህዝብ የሚወግኑ እጩዎችን የሚመለከታቸው አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። በመሆኑም በተጠቀሱት ቀናት እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑና ለህገ መንግስቱ ታማኝ የሆኑ እንደሁም ፍላጎት ያላቸውና ከደንብ መተላለፍ ውጭ በወንጀል ያልተከሰሱ እጩዎችን መጠቆም ይቻላል ብለዋል። እጩዎች በህግና መሰል ሙያ የተመረቁ፣ የአስፈፃሚ አካላት በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን በደል የሚመክቱና የዜጎች ደህንነት የሚያሳስባቸው መሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የህፃናትና ሴቶች ኮሚሽነር እጩ አቅራቢ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ብርሃኑ አበበ በበኩላቸው የሚጠቆመው የህፃናትና ሴቶች ኮሚሽነር "ለሰብዓዊ መብት የሚቆረቆር መሆን አለበት" ብለዋል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች የሚጠቆሙበትና ማሟላት የሚገባቸው መስፈርት ከእምባ ጠባቂ እጩዎች ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑንም አስረድተዋል። የተቋማቱን መስፈርት የሚያሟላ፣ ለመምራት ብቃት፣ ዝግጁነትና ፍላጎት ያለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ካለ የሲቪክና ሙያ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጥቆማ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እጩ አቅራቢ ኮሚቴ የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ፤ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ 19 አባላት አሉት። የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ደግሞ የምክር ቤት አፈ ጉባኤን በሰብሳቢነት የሚይዝ ሆኖ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤን ጨምሮ ሰባት አባላት እንዳሉት ተገልጿል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፎካካሪ ፓርቲ ባለመኖሩ በሁለቱም ኮሚቴዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በአባልነት ማካተት አልተቻለም ተብለዋል። ከተጠቆሙ እጩዎች በኮሚቴዎቹ የሁለት ሶስተኛ ድምጽ የሚገኙት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የምክር ቤቱን ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ሲያገኙ ሹመታቸው ይጸድቃል። የሰብዓዊ መብት እጩዎችን በስልክ- 011-154-39-65፣ በፋክስ 011-124-11-38 ወይም በኢ-ሜይል humanrightethio@gmail.com እና በፖስታ ሳ. ቁጥር 80001 መጠቆም ይቻላል። በተመሳሳይ የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም እጩዎችን በስልክ ቁጥር 011-124-10-36 በፋክስ 011-124-11-38 በፖስታ ሳ. ቁጥር 80001 እነዲሁም በኢ-ሜይል obudosmanethio@gmail.com ጥቆማ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም