በጭሮ ከተማ 27 ኪሎ ሜትር የተሽከርካሪ መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቃ

60
ጭሮ 5/10/2010 በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ እየተገባበደ ባለው በጀት ዓመት ከተጀመሩ የመሰረተ ልማቶች ውስጥ የ27  ኪሎ ሜትር  የተሽከርካሪ መንገድ ተገንብቶ  ለአገልግሎት በቃ፡፡ በከተማው አስተዳደር ጽህፈት ቤት  የመሰረተ ልማት የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አስራት መስፍን እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እስካሁንም ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍን  27  ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ የመኪና መንገድ ግንባታ በእቅዱ መሰረት በማከናወን አገልገሎት መስጠት ጀምሯል። በከተማዋ የመንገድ ዳር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ግንባታዎችም ስራ 90 በመቶ መከናወኑን ያመለከቱት አቶ አስራት እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የተጠናቀቁትና በሂደት ላይ የሚገኙት የመሰረተ ልማት ስራዎች  ከተማዋን ውብ ከማድረግ ባለፈ ለማህበራዊ አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። "በግንባታውም በ18 ማህበራት የተደራጁ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ተጠቃሚ ሆነዋል "ብለዋል የስራ ሂደቱ ባለቤት። ከከተማው ነዋሪዎች መካከል  አቶ መሀመድ እንድሪስ በሰጡት አስተያየት የጭሮ የውስጥ ለውስጥ መንገድ በክረምት ጭቃ በበጋ ወቅት ደግሞ በአቧራ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ በመሰራቱ እፎይታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የመንገድ ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ እየጠየቁ ምላሽ ሳያገኝ  ለዓመታት መቆየቱን ያመለከቱት ደግሞ ሌላው  ነዋሪ አቶ ስለሺ ታዬ መንግስት ናቸው፡፡ " በጥልቅ ተሀድሶ በተወሰደው እርምጃ ችግራችን ሊፈታ ችሏል" ብለዋል። ወይዘሮ ስንዱ አፈወርቅ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ከአሁን በፊት በከተማዋ  የጎርፍ ማስወገጃ ቦዮች በተገቢው ስለማይሰሩ  ውሃ መንገድ ላይ እየተኛ እንደልብ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው አሁን በመስተካከሉ ችግሩ እንደሚቃለልላቸው ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም