ጎሽ ሜዳ የቧንቧና ፕላቲክ ማምረቻ ድርጅት ተመረቀ

164
ደሴ ኢዜአ ሐምሌ 27/2011  በደሴ ከተማ በ63 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ጎሽ ሜዳ የቧንቧና ፕላቲክ ማምረቻ ድርጅት ዛሬ ተመረቀ። በምረቃው ስነስርዓት ወቅት  የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ  አቶ መሃመድ አህመድ እንደገለጹት ጎሽ ሜዳ ቧንቧና ፕላስቲክ ድርጅት በ2009 ዓ.ም በአማራ ክልል በአዋጅ የተቋቋመ ነው ፡፡ "ዓላማውም በግብአት እጥረት ምክንያት የተከሰተውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት ፤ ግብርናውን ለማዘመንና ለኮንስትራክሽን የሚያገለግሉ ቱቦዎችን ለማምረት ነው "ብለዋል፡፡ እንደ አቶ መሃመድ ገለጻ የአማራ ህንጻ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ የአማራ ዉሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት በጋራ የግብዓት እጥረት ለመፍታት  ያቋቋሙት ነው ፡፡ ፋብሪካው  200 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ  ፕሮጀክት ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታው በ63 ሚሊዮን ብር ወጪ ተጠናቅቆ የሙከራ ምርት ጀምሯል ። ፋብሪካው በሰባት የማምረቻ ማሽኖች እየታገዘ በሰዓት ከ3 ሺህ ቶን በላይ ከ16 እስከ 630 ሚሊ ሜትር ስፋት ያላቸው ቱቦዎችን ያመርታል፡፡ የፋብሪካው ምርቶች ለመጠጥ ውሃ፣ ለመስኖ፣ ለኤሌክትሪክ ገመድ ሽፋን፣ለፈሳሽ ቆሻሻ ማስተላለፊያ፣ ለውሃ መሸጋገሪያ የሚሆኑ  እንደሚያመርት ተገልጿል። ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ለ250 ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን እስካሁን ለ40 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል ተብሏል፡፡ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢና የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ በበኩላቸው ምርቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ እንደሚያቀርብ አመልክተው በቀጣይም  ለአፍሪካ ሀገራት  በጥራትና በብዛት ለማቅረብ መታቀዱን አስታውቀዋል። በግብዓት እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መስተጓጎልና የመስኖ ፕሮጀክቶች መጓተት ችግር የመፍታት አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል ። እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ የችግኝ ማፍያና ሌሎች የተለያዩ ፕላስቲኮችንም ያመርታል፡፡ "የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካም ክልሉ ድጋፍ ፣ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል "ብለዋል፡፡ በደሴ ከተማ የሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ 015 ቀበሌ ነዋሪ ሼህ እንድሪስ ሲራጅ በሰጡት አስተያየት በአካባቢቸዉ የተሰራው ፋብሪካ ለልጆቻቸው የሥራ እድል መፍጠሪያና ለአካባቢ ልማት የሚጠቅም በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ "ፋብሪካው ሀብታችን በመሆኑ እንክብካቤና ከለላ በማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን "ብለዋል ። በምረቃ ስነ ስረዓት ወቅት ከአማራ ክልልና ከምስራቅ አማራ ዞኖች የተወጣጡ አመራሮች የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም