በኢሉአባቦር ዞን አደረጃጀቶችና ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ ቀን ለተከሏቸው የዛፍ ችግኞች ጥበቃና እንክብካቤ እያደረጉ ነው

200

መቱ ሐምሌ 27/ 2011 በኢሉአባቦር ዞን ሦስት ወረዳዎች የሚገኙ የአርሶአደር አደረጃጀቶችና ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ ቀን ለተከሏቸው የዛፍ ችግኞች ጥበቃና እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ገለጹ።

ዞን ሦስት ወረዳዎች የሚገኙ የአርሶአደር አደረጃጀቶችና ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ ቀን ለተከሏቸው የዛፍ ችግኞች ጥበቃና እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን ገለጹ።

በአልጌ ሳቺ ወረዳ የአልጌ ከተማ ነዋሪ አቶ አባድር ታዬ እንዳሉት የእስልምና ሃይማኖት ተቋም ኮሚቴ አዋቅረው ለተከሉት ሰባት ሺህ በላይ ችግኞች እንክብካቤ እያደረጉ ነው።

“እኔም የኮሚቴው አባል ነኝ” ያሉት አቶ አባድር፣ ችግኞቹን ዙሪያቸውን በመከለልና የጥበቃ ሠራተኛ በመቅጠር እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የከተማው ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የአረንጓዴ አሻራ ዛፍ ችግኝ ጥበቃና እንክብካቤ ኮሚቴ አባል አቶ ዱጉማ ከባ በበኩላቸው ከስምንት ሺህ በላይ የዛፍ ችግኞችን በመትከል ከሰውና እንስሳት ንክኪ ከልለው እየጠበቁ ነው።

በበቾ ወረዳ ፉጎ ሳርዶ ቀበሌ ቀበሌ አርሶአደር ደሳለኝ አረጋ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ከሚገኙ ሌሎች 180 አርሶአደሮች ጋር በመሆን ከጉድጓድ ቁፋሮ አንስቶ እስከ እንክብካቤ በጋራ መስራታቸውን ይናገራሉ።

“ችግኞቹ ሳይተከሉ አስቀድሞ አጥር ሰርተናል” ያሉት አርሶ አደሩ፣ ማረፊያ ሰርተው በአካባቢው እያደሩ ጭምር ጥበቃና እንክብካቤ እያደረግኩኝ ነው ብለዋል።

የአካባቢያቸውን ወጣቶች በማስተባበርችግኞቹን በመከለልና አረም በማጥፋት ሙሉ ለሙሉ እንዲፀድቅ በመሥራት ላይ እንደሆነ የተናገረው ደግሞ በያዮ ወረዳ መጌላ ቀበሌ ወጣት ምትኩ ጃለታ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር አንድነታቸውን ይበልጥ እንዳጠናከረ ገልጾ፣ ይህም በሌሎች የልማት መስኮችና የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ መነቃቃት እንደፈጠረባቸው ተናግሯል።

በኢትዮጵያ ብዘሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት የመቱ ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ናኦል ባዩ እንዳሉት የማዕከሉ ሠራተኞች የያዮ ተፈጥሮ ደን በሚገኝበት አካባቢ በአረንጓዴ አሻራ ቀን 10ሺ 200 ችግኞች ተክለዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ቡና፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ለገሰ እንዳሉት በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተተከሉት ችግኞች ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ከማህበራትና ተቋማት ጋር ርክክብ እየተደረገ ነው።

የግብርና ባለሙያዎችም ችግኞቹ በተተከሉባቸው አካባቢዎች በመሰማራት ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ 13 ወረዳዎች በአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ14 ሚሊዮን 500ሺ በላይ የዛፍ ችግኞች ተተክለዋል።