ኮሌጁ በሰባት የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 667 ተማሪዎች አስመረቀ

66
ሚዛን ሐምሌ 27 /2011 የአማን ጤና ሣይንስ ኮሌጅ በሰባት የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 667 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ። ከተመራቂዎቹ 485ቱ ሴቶች ናቸው። የኮሌጁ ምክትል ዲን እስራኤል ዳርኪያብ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ተማሪዎቹ የተመረቁት ከደረጃ ሁለት እስከ ደረጃ አራት በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተሰጣቸውን ትምህርት በማጠናቀቃቸው ነው። ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀት ኅብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። አገሪቱ ያቀደቻቸውን የጤና ግቦች ለማሳካት መካከለኛ የጤና ባለሙያዎች ሚናቸው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ አቶ መስፍን በቀለ ናቸው። የጤና ሙያ አክብሮት፣ ትህትናና ግብረ ገብነት ስለሚጠይቅ ተመራቂዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ሙያው ያስተማራቸውን አገርና ወገን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። በሜዲካል ላቦራቶሪ ዘርፍ የተመረቀው ሥርዓት ሲኖር በሦስት ዓመታት የኮሌጅ ቆይታዬ በቂ ሙያዊ ዕውቀት አግኝቻለሁ ብሏል። በተግባርና በንድፈ ሀሳብ በቀሰመው ዕውቀትም ኅብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቱንም ተማሪ ሥርዓት ተናግሯል። ኮሌጅ ከ1999 ጀምሮ ሥልጠና በመስጠት ላይ ነው። በደቡብ ክልል ከሚገኙ አራት የጤና ሳይንስ ኮሌጆች አንዱ መሆኑም ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም