የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን የማጣርያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ያደርጋል

83
ሀምሌ 27/2011 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ዋንጫ (ቻን) የማጣርያ የመልስ ጨዋታውን ነገ በድሬዳዋ ስታዲየም ነገ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ከጅቡቲ አቻው ጋር ያደርጋል። በካሜሮን አስተናጋጅነት ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የቻን ውድድር በጥር ወር 2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ በብሔራዊ ቡድን ተካተው የሚጫወቱበት ነው። የአፍሪካ አገራትም በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በጅቡቲ ሀሰን ጉሌድ ኦብቲዶ አድርጎ በአስቻለው ታመነ የፍጹም ቅጣት አንድ ጎል በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉንም አስፍቷል። ብሔራዊ ቡድኑ የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ  በድሬዳዋ ከሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ልምምድ እያደረገ ይገኛል። የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታ በተደረገበት ማግስት በባቡር ተጉዞ ድሬዳዋ በመግባት ልምምድ እየሰራ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በድምር ውጤት ጅቡቲን ካሸነፈ ቀጣይ ጨታውን መስከረም ወር 2012 ዓ.ም ከሩዋንዳ አቻው ጋር የሚያደርግ ይሆናል። የሩዋንዳ አቻውንም በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በቻን ውድድር ላይ መሳተፉን ያረጋግጣል ማለት ነው። የ30 ዓመቱ ሶማሊያዊ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀሰን መሐመድ ሀጂ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል። በቻን ውድድር ለመሳተፍ በምዕራብ ዞን ኤ፣ በምዕራብ ዞን ቢ፣ በሰሜን ዞን፣ በማዕከላዊ ዞን፣ ማዕከላዊ ምስራቅ ዞን እና ደቡብ ዞን ተከፍሎ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተደረጉ ይገኛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ ያለበት ዞን ማዕከላዊ ምስራቅ ዞን ነው። በአጠቃላይ በስድስቱ ዞኖች እስከ ጥቅምት ወር 2012 ዓ. በሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች 15ቱ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ይሆናል። በስድስተኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ዋንጫ (ቻን) ውድድር አዘጋጇን አገር ጨምሮ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ። ስድስተኛውን የቻን ውድድር ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ እድል ተሰጥቷት የነበረ ቢሆንም በልምምድ ሜዳና በስታዲየሞች ግንባታ ዝግጅት ማነስ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ አስተናጋጅነቱን ከኢትዮጵያ ነጥቆ ለካሜሮን መስጠቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመራ ሲሆን የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በፈረንሳዊው የ37 ዓመት አሰልጣኝ ጁሊያን ሜት ይሰለጥናል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም