የሞቃዲሾ ከተማ ከንቲባ በሽብር ጥቃት ህይወታቸው አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሞቃዲሾ ከተማ ከንቲባ በሽብር ጥቃት ህይወታቸው አለፈ

ሀምሌ 26/2011 የሞቃዲሾ ከተማ ከንቲባ ህይወታቸው ያለፈው ባለፈው ሳምት በጽህፈት ቤታቸው በተፈፀመ የቦንብ ጥቃት ቆስለው ህክምና ሲደረግላቸው ከቆየ በኋላ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ከጥቃቱ በኋላ በኳታር ህክምና ሲደረግላቸው የነበሩት የከንቲባ አብዲራህማን ኦማር ኦስማን ህይወት ማለፍን የሶማሊያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አረጋግጠዋል ሲልም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በብሪታኒያ የተወለዱት ከንቲባ ኦስማን የሌበር ፓርቲ አባል ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በጦርነት የተጎሳቆለችውን ሀገር መልሶ ለመገንባት አስተዋፅኦ ለማድረግ በማሰብ ወደ ሶማሊያ እንደተመለሱ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሙሃመድ አብዱላሂ የተሰውትን ከንቲባ በመላ ሀገሪቱ ታስበው ይውሉ ዘንድ የሶስ ቀናት ብሄራዊ የሃዘን ቀን ያወጁ ሲሆን የሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ መታዘዙን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ከንቲባው ኦስማን በ2010 ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሶማሊያ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በዚህ ዓመት መጨረሻ ደገሞ የሞቃዲሾ ከንቲባ በመሆን እያገለገሉ ባለበት ሰአት ህይወታቸው ማለፉን ሲጂቲኤን አስታውሷል፡፡