የጤና መሰረተ-ልማትን ለማስፋት የሚያስችል የጤና ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ ነው

87
ሐምሌ 25 / 2011 (ኢዜአ) የጤና መሰረተ-ልማትን ለማስፋት በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ። የጤና ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት ክንውኑን አስመልክቶ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በሰጡት መግለጫ በአገር አቀፍ ደረጃ 21 ስፔሻላይዝድ እና 92 ጠቅላላ ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ ነው። 289 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣ ሶስት ሺህ 956 ጤና ጣቢያዎች እና 18 ሺህ 816 ጤና ኬላዎችም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ በተጨማሪ አንድ ስፔሻላይዝድ፣ ሶስት ጠቅላላ እንዲሁም 99 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ግንባታ እየተከወነ መሆኑንም ተናግረዋል። 62 ጤና ጣቢያ፣ 499 ጤና ኬላዎችን ከክልሎችጋር በመቀናጀት ግንባታቸው እየተከወነ መሆኑም እንዲሁ። በሁለተኛው ትውልድ የጤና ኬላ ዲዛይን መሰረት 100 ጤና ኬላዎችን ለመገንባት ከክልሎች የ74 ቀበሌዎች ቦታ መረጣ ተካሂዶ በጨረታ ሂደት እንደሚገኙም ገልፀዋል። ግንባታዎቹ እስከ 2012 በጀት ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቁም ተገልጿል። በበጀት ዓመቱ የ895 አምቡላንሶች ግዥ መፈፀሙንና የአንድ ሺህ 800 አምቡላንሶች ግዥም በክትትል ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚረዱ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በ23 ከተሞች ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሆኑ መንገዶች ቀን በየወሩ በማካሄድ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርመራ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል። ለካንሰር በሽታ የጨረር ህክምና ማስፋፊያ ማዕከላት በሀሮማያ፣ ጅማ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች የመሳሪያ ተከላ ስራ መጠናቀቁንም አስረድተዋል። የጎንደር፣ ሀይደር፣ ሃዋሳና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰር የህክምና ማዕከላት ግንባታ 90 በመቶ መድረሱንም ነው የገለጹት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም