የገንዘብ አቅርቦትና የአሰራር ችግር የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ዕድገት እየተፈታተነ ነው

94
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 አነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን በክልሎች ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት በገንዘብ አቅርቦትና በአሰራር ችግር ሳቢያ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ የክልል ቢሮዎች አስታወቁ። እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት በዘርፉ ለሚሳተፉ አካላት ለማሽንና ለሌሎች መሳሪያዎች መግዣ ከተመደበው ስምንት ቢሊዮን ብር የሊዝ ካፒታል መጠቀም የተቻለው 15 በመቶውን ብቻ ነው። በአማራ፣ ትግራይና ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘርፉ ማሰማራት እንዲቻል የማደራጀት ሥራዎች ተከናውነዋል። ሆኖም በገንዘብ አቅርቦትና በአሰራር ችግር ሳቢያ ግለሰቦቹን በተቻለ ፍጥነት ወደሥራ ማስገባት እንዳልተቻለ የየክልሎቹ የዘርፉ ቢሮ ኃላፊዎች ለኢዜአ ሪፖርተር ገልፀዋል። መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ማብቂያ ከ27 ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም አቅዷል። በእስካሁኑ ትግበራ ማሳካት የተቻለው ከ12 ሺህ እንደማይበልጥ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል። የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሙሐመድ "በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፍ ለተደራጁ አካላት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች በወቅቱ አይደርሱም፤ ይህም ዘርፉን ወደ ኋላ እየጎተተው ነው፤" ብለዋል። የኤሌክትሪክ ችግር፤ እንዲሁም የገንዘብ አቅርቦት በሚፈለገው ጊዜ አለመድረስ በአማራ ክልል የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፍ ዕድገት ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተማከለ አሰራር የተፈቀደውን ገንዘብ በማዘግየት ወጣቶችን ተስፋ እያስቆረጣቸው ስለሆነ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል። የደቡብ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሸቦ ኡሊሶ በበኩላቸው አምራቾች ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ማሽን በሚፈለገው ጊዜ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልፀዋል። "የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ማስኬጃ ገንዘቡን በወቅቱ አይለቅም፤ ዕቃ አቅራቢ ድርጅቱም ክልሉን ዞር ብሎ አይቶት አያውቀም" ሲሉም አቶ አሸቦ ገልፀዋል። በዘርፉ ለሚሳተፉ አካላት ማሽኖችና ሌሎች መሳሪያዎች መግዣ የተመደበው የሊዝ ካፒታል መዘግየትና የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት ዘርፉን እያቀጨጩት ነው ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ የማኑፋክቸሪንግ ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማይ ገብረኪዳን ናቸው። እነዚህ ችግሮን በዘላቂነት ለመፍታትና የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፉን ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል። የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንዳሉት በዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ዘንድ ያለው የግንዛቤ እጥረት እና ቁርጠኝነት ማነስ በዘርፉ የሚታየው ዋናው ችግር ነው። ማሽነሪዎችና ሌሎች መሳሪያዎች መግዣ የተመደበው የሊዝ ካፒታል በሚቻለው ፍጥነት እንደማይለቀቅ፣ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ የሚያበድሩ ክልሎች ላይ ያሉ የፋይናንስ ተቋማትም በቂ ብድር እንደማይሰጡ ተገንዝበናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ችግሮችን ለመፍታት ከፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልፀዋል። "በ2010 በጀት ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር የሊዝ ካፒታል ቢመደብም መጠቀም የተቻለው 15 በመቶ ብቻ ነው፤ ይህ የሆነው ግን በልማት ባንክ ችግር ብቻ አይደለም፤ የቅንጅት ማነስም ለተፈጠረው ችግር ሌላው ምክንያት ነው። ምክንያቱም በቂ የገንዘብ አቅርቦት እያላቸው ወደሥራ ያልገቡ አሉ፤" ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም