ምርምሮችና አዳዲስ ሃሳቦች በማኅበረሰቡ መመራት እንዲችሉ ሆነው መቀረጽ አለባቸው

64
ሀምሌ 23/2011 በከፍተኛ  የትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ማኅበረሰብ  አቀፍ አገልግሎቶች በማኅበረሰቡ መመራትና መተዳደር እንዲችሉ ተደርገው መቀረጽ እንዳለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።
"በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት መስጠት ይቻላል" በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ የሁለት ቀናት ውይይት ዛሬ ተጀምሯል። የሚኒስቴሩ የምርምና አካዳሚ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ ሚጀና እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምርምሮችና አዳዲስ ሃሳቦች ማህበረሰቡ በባለቤትነት እንዲመራቸውና ወደ ተግባር እንዲለወጡ በስራው ተሳታፊ ማድረግ ይገባል። በአገሪቱ አሁን ባለው አካሄድ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ምርምሮችም ይሁን አገልግሎቶች ህብረተሰቡ ስለማይሳተፍባቸው የሚፈለገውን ውጤት 'እያመጡ አይደለም' ብለዋል። በዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች በሚወጡ ምርምሮችና አገልግሎቶች ላይ ማህበረሰቡ ከእቅድ ጀምሮ እኩል ተሳታፊ መሆን አለበት ነው ያሉት። በአገሪቱ  ወጪ ተደርጎባቸው የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮችም ከመደርደሪያ ወርደው የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚሰጡ ማህበረሰብ አቀፍ ግልጋሎቶች የሰጪና የተቀባይ አይነት አሰራር ሊኖር አይገባም። ይህ ቅንጅት ችግሮች በአካባቢው ህብረተሰብ በሚገባ ተለይተው መፍትሄ እንዲያገኙና አጥኚዎችም ለችግሮቹ የተሻለ መፍትሄ እንዲሰጡ እንደሚያግዝም አክለዋል። በሌላ በኩል በተለይ ችግር ፈቺ የሆኑ የማህበረሰብ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲተገበሩ  ተቋማዊ አሰራር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ኤባ ጠቁመዋል። ለዚህም መመሪያ ተዘጋጅቶ ለሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መላኩን ገልጸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መመሪያውን በአግባቡ ተግባራዊ ማደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል። እየተካሄደ ያለው ውይይትም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚያስችል ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል። በውይይቱ ከአሜሪካው ኮሎራዶ ዩኒቨርሲቲ ሃላፊዎች ጋር የልምድ ልውውጥ የሚካሄድ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሃለፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም