በአዲስ መልክ በተገነቡት የአውቶቡስ መጠበቂያ ሼዶች የስራ እድል ተፈጥሮልናል-ተጠቃሚ ሴቶች

41
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 በመዲናዋ በአዲስ መልክ በተገነቡት የአውቶቡስ መጠበቂያ በተፈጠረላቸው ሼዶችን የማጽዳት  የስራ እድል ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን በማሕበር የተደራጁ ሴቶች ገለጹ። በቀጣዩ በጀት ዓመትም ተጨማሪ 500 የአውቶቡስ ማቆሚያ ሼዶች የሚገነቡ ሲሆን የጽዳቱ ስራ በተመሳሳይ ለተደራጁ ሴቶች እንደሚሰጥም ነው የከተማዋ ትራንስፖርት ባለስልጣን ያስታወቀው። የስራ እድሉ ከተፈጠረላቸው ሴቶች መካከል ወይዘሮ መስከረም ሰቦቃ እንደሚሉት በማሕበር ተደራጅተው ይሕንን ስራ ከመጀመራቸው በፊት የተለያዩ ተባራሪ ስራዎችን ሲያከናውኑ ነበር። ይሕ ተባራሪ ስራ ሊኖርም ላይኖርም ስለሚችል አስተማማኝ አለመሆኑንና ተሯሩጦ ለእለት ጉርስ የሚሆን እንጂ ስለነገ የሚታሰብበት እንዳልነበር ያነሳሉ። ሌላው ተጠቃሚ ወይዘሮ የሺዓለም ተምትም በበኩላቸው ከዚህ በፊት በየሰው ቤት ልብስ በማጠብና እንጀራ በመጋገር ይተዳደሩ እንደነበርና አሁን ግን ከጽዳት ስራው በወር 1ሺህ 900 ብር እንደሚከፈላቸው ነው የሚገልጹት። ከዚህ ገቢም በተደራጁበት ማሕበር በኩል የባንክ ደብተር ተከፍቶላቸው በየወሩ 500 ብር ለመቆጠብ መስማማታቸውንና  የመጀመሪያውን ወር ቁጠባቸውን ማስቀመጣቸውን ነው ያመለከቱት። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አስማረ በበኩላቸው በመዲናዋ ካለው የትራንስፖርት ፍላጎት አንፃር መንግስት ወደፊት የብዙሃን ትራንስፖርት ልማትን ይከተላል። በዚህ መሰረትም የብዙሃን ትራንስፖርት መጠበቂያ ሼዶችን ምቹና ጽዱ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ 250 ሴቶች  የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመትም የሚገነቡት 500 ተመሳሳይ  ሼዶች ለነዚሁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስራ ለመፍጠር እንደሚቻል ተጠቁሟል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም