በየመን የባህር ዳርቻ 46 ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸው መረጋገጡን ተከትሎ መንግስት ሀዘኑን ገለፀ

64
በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተዘጋጀ ዜና መግለጫ ሰኔ 5 /2010 በየመን የባህር ዳርቻ 46 ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተረጋገጠ የኢፌድሪ መንግስት በየመን የባህር ጠረፍ የደረሰን የጀልባ አደጋ አስመልክቶ ወደ ስፍራው ሰዎችን በማሰማራት፣ በአካባቢው የሚገኙ ኤምባሲዎቻችንን በማንቀሳቀስ እና የመን እና አዲስ አበባ የሚገኘው የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመሆን አደጋውን በቅርበት ሲከታተለው ቆይቷል፡፡ በተደረገው ክትትል 46 ያህል ዜጎቻችን በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ለመረዳት ተችሏል። መንግስት ከተባበሩት መንግስታት የፍልሰት ድርጅት  እንዲሁም ከአደጋው የተረፉ ወገኖች ጋር ባደረገው ክትትል ለመገንዘብ እንደተቻለው 100 ያህል ኢትዮጵያውያንን የጫነች ጀልባ ከቦሳሶ ሶማሊያ ተነስታ ስትጓዝ ካደረች በኋላ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም የመን የባህር ጠረፍ ላይ ስትደርስ በደረሳባት አደጋ 46 ሰዎች ሲሰጥሙ 15 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ቀሪዎቹ  ከአደጋው የተረፉ 39 ወገኖቻችን በአከባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር የመን ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና ድጋፍ እንዲስጣቸው እያደረጉ ነው፡፡ መንግስት በዜጎቻችን ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ በአሁኑ ሰዓት መንግስት በተለያየ ምክንያት በውጪ ሀገራት በስደትና በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ባሉበት አገር ከመደገፍ በተጨማሪ ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት በሚያደርግበትና በተጨባጭም ውጤቶች እየተመዘገበ ባለበት በዚህ ጊዜ ይህ አሳዛኝ አደጋ መከሰቱ ህጋዊ ያልሆነ ሰዎች ዝውውር እንቅስቃሴው ምን ያህል ውስብስብ እና በወገኖቻችን ደህንነት ላይ የተጋረጠ አደጋ እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል፡፡ በመሆኑም መላ የሀገራችን ህዝቦች እና በተለይም የዚህች ሀገር ዋና ባለቤት የሆኑት ወጣቶቻችን የራሳቸውንም ሆነ የወገኖቻችን ህይወት ከጥፋት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከጎናችን በመቆም አስተዋፅኦ እንድታደርጉ መንግስት ሀገራዊ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ሰአት መንግስት በውጪ ሀገራት በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖች ሁሉ በወገናቸው መሀል ተከብረው መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት በሚያደርግበትና በተጨባጭም ውጤቶች እየተመዘገቡ ባለበት በዚህ ጊዜ ይህ አሳዛኝ አደጋ መከሰቱ የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር እንቅስቃሴው ምን ያህል ጥልፍልፍና አሳሳች የወንጀል ድር እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል፡፡ መንግስት ማረጋገጥ እንደቻለው ጀልባዋ የመስመጥ አደጋ የደረሰባት ከመጫን አቅሟ በላይ የሆነ ተሳፋሪ ይዛ በመጓዟ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ወቅትም ተሳፋሪዎቹ ከጸጥታ ሀይሎች እና ከሰው እይታ ለመራቅ በማሰብ ከየብስ አቅራቢያ ርቀው ይጓዙ ስለነበር የህይወት ማትረፍ ሙከራው ውጤት እንዳላመጣ ከአለም አቀፍ አጋሮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህንን የወገኖቻችንን የመኖር መብት እና አደጋ ውስጥ የከተተ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመቅረፍ እና የድርጊቱን ተዋንያን ለፍርድ ለማቅረብ በመንግስት በኩል በጥናት ላይ የተደገፈ ስራ ለመስራት አስፈላጊው ሁሉ እየተደረገ ሲሆን ይህ እንቅስቃሴም ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ማንም ከመኖር የሚቀድም አላማ የለውም፡፡ መንግስት በሀገር ቤት ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ሀገራችን ለሁላችንም የለውጥ መሰረት እንድትሆን ያለመታከት እየሰራ ቢሆንም ችግሮች ሁሉ በአንድ ጀምበር የሚፈቱ ባለመሆናቸው ለዘላቂው ስኬታችን እና በምንም ለማይተካው ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ልእልና በጋራ ለመስራት የምንገደድበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ በመሆኑም ሰውን የሚያህል ክቡር ፍጡር እንደ ተራ እቃ አነባብረው በመጫን የግላቸውን ኑሮ ለማደላደል በሚሮጡ ኢ-ሰብአውያን ውትወታ እና አማላይ ገለጻ ላለመታለል ለራሳችን ቃል ልንገባ ይገባናል፡፡ የኢፌድሪ መንግስት ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በቀጥታ በመገናኘት ሌሎች መረጃዎችን የሚያደርስ ሲሆን ለመላ ኢትዮጵያውያን መጽናናትን- ላለፉት ወገኖችም እረፍትን ይመኛል፡፡ አሁንም በድጋሚ በአደጋው ባጣናቸው ዜጎች አሳዛኝ ሞት መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እንደገና ይገልጻል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም