ሰሜን ኮሪያ የኑክሌየር ማበልጸግ መርኃ ግብሯን እንደምታቆም ኪም ጆንግ ተናገሩ

98
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 ሰሜን ኮሪያ የኑክሌየር ማበልጸግ መርኃ ግብሯን እንደምታቆም ኪም ጆንግ በሲንጋፖር ዳግም ቃል ገቡ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ የሲንጋፖር ታሪካዊ ስብሰባቸውን ከሰዓታት በፊት አጠናቀዋል። ሁለቱ መሪዎች በኮርያ ልሳነ ምድር የኑዩክሌር ማበልጸግ መርኃ ግብርን ለማስቆምና ሠላምን ለማስፈን በሚቻልበት ጉዳይ መምከራቸውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል። ዶናልድ ትራምፕ ከኪም ጆንግ ዩን ጋር "የተለየ ወዳጅነት እንፈጥራለን" ሲሉ በስብሰባው ያላቸውን እምነት ከወዲሁ መግለጻቸው ይታወሳል። ሰሜን ኮርያ እንደ አውሮፓውያኑ አቀቆጣጠር በ1974 በኪም ሁለተኛ ጀምሮ የኑዩክሌር መርኃ ግብሯን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከአሜሪካና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እሰጣ ገባ ወስጥ ገብታለች። ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲም ሰሜን ኮርያ ኑክለር ማበልጸግ የሚከለክለውን ስምምነት በመጣስ፤ ከስምምነቱ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ያለቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መውጣቷን ገልጿል። ከዛም በኋላ በተለያዩ ጊዜያት የኑክሌር ግንባታ መርኃ ግብሯን አጠናክራ በመቀጠል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 በወር ስድስት የኑክለር ቦምብ ማበልጸግ የሚያስችል አቅም መገንባት ችላለች። ያም ብቻ ሳይሆን ይኸው የኒዩክሌር ቦምብ የአሜሪካን ምድር ላይ መድረስ የሚችልና እጅግ ከባድ መሆኑን ገልጻለች፤ ይህም ደግሞ ኃያሏን  አሜሪካን በእጅጉ ያስቆጣ ድርጊት ሆኖ ቆይቷል። ይህንንም የኑክሊየር መርኃ ግብር ከመንግሥታቱ ድርጅት ጀምሮ ከጎረቤት አገሮቿ የእንደራደርና እንወያይ ጥሪ ቢቀርብላትም በማን አለብኝነት ስሜት ስትገፋበት መቆየቷን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። ይህንንም ተከትሎ በአሜሪካ ፊት መሪነት በርካታ አገራት ይህንን ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚጥሰውን የሰሜን ኮሪያ ድርጊት ለመግታት በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ማእቀብም ሲጥሉባት ቆይተዋል። ለአብነትም የነዳጅ ዘይት ለውጭ ገበያ እንዳታቀርብ፤ የጦር መሣሪያ ግዥ እንዳታካሂድና ሌሎችም መሰረታዊ ምጣኔ ኃብታዊና የንግድ እገዳ ማዕቀብ ኅብረተሰባዊቷ ሰሜን ኮርያ ላይ ጥለውባታል። እንዲህ ያሉ እርምጃዎች አልበግራት ያለው ሰሜን ኮሪያም በተለይም ከጥቂት ወራቶች በፊት አቋሟን በመለወጥ ከደቡብ ኮሪያና ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ፍላጎቷን ስታሳይ ቆይታለች። ከወራት በፊትም ታሪካዊ የተባለውን ጉዟቸውን ወደ ደቡብ ኮሪያ በማምራት ከፕሬዚዳንት ሙን ጃኤ ጋር መወያየት ችለዋል፤ በዚህም የኑክሌር መርኃ ግብሩን ለማቆም ተስማምተዋል። እንዲያውም ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በተገኙበት የኑክሌር መርኃ ግብር የሚካሄድበትን መንደር በድማሚት ማፈራረሷን ተከትሎ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርምጃው በእጅጉ ተወድሷል። ከዛም በኋላ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር መነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ከትላንት ጀምሮ በሲንጋፖር ተገናኝተው ታሪካዊው የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ ከሰዓታት በፊት ተጠናቋል። በብዙዎች ተመራማሪዎች ዘንድ ተስፋ የጣለበት ይህ ስብሰባ የኮርያ ልሳነ ምድር ከኑዩክሌር ነጻ በማድረግ የአሜሪካ ጥቅም የተከበረበት ሆኖ ስብሰባው ተጠናቋል የሚል ግምት እየተስተጋባበት ይገኛል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ ከሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጁንግ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። መሪዎቹ ከውይይቱ በኋላም አሜሪካ በኮሪያ ልሳነ ምድር ከዚህ በፊት ከደቡብ ኮሪያ ጋር ስታደርገው የቆየችውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማቆም መስማማታቸው ተገልጿል። በዚህም ሰሜን ኮርያ የኑክሌየር ማበልጸግ መርኃ ግብሯን እንድታቋርጥ በመርህ ደረጃ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመው ይህም ቢሆን በሂደት በተግባር የሚታይ መሆኑን ነው ያሰመሩበት። ስለዚህም አሜሪካ በሰሜን ኮርያ ላይ የጣለችው የምጣኔ ኃብት ማዕቀብ ጸንቶ እንደሚቆይና አገሪቱ ከመርኃ ግብሩ እራሷን ነጻ ስታደርግ ሙሉ በሙሉ እንደሚነሳላት አረጋግጠዋል። ያም ሆኖ ሰሜን ኮርያ እራሷን ከመርኃ ግብሩ ማበልጸግ ነጻ ካደረገች ምን አይነት ዋስትና ይሰጣታል? ተብሎ ለተጠየቁት ጥያቄም ይህንንም አብረን የምናየው  ጉዳይ ነውብለዋል ፕሬዚዳንቱ። የኑክሌር መርኃ ግብሩን ማስቆምን በተመለከተ ረጅም ጊዜ ይፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ ከኪም ጋር ቀጣይ ስብሰባ ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል። ጎን ለጎንም በአገሪቱ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝና በሌሎች ጉዳዮችም ላይ መወያየታቸውን ፕሬዘዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል። ሁለቱ መሪዎች በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ፊት ለፊት የጋራ ሰነድ አውጥተው ፈርመዋል፤ ይሁንና ሰነዱ አዲስ ነገር አልያዘም የሚል ሂስ እየቀረበበት ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም