በዛሬው ዕለት 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የችግኝ ተከላ ዘመቻ እየተካሄደ ነው

86

ሀምሌ22/2011(ኢዜአ) በአረንጓዴ አሻራ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በሁሉም የአገሪቱ  ክፍሎች  የችግኝ ተከላ ዘመቻ እየተካሄደ ነው። በዛሬው እለት በመላው ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የችግኝ ተከላውን እያከናወኑ መሆኑና መረጃዎች ወደማዕከል እየደረሱ መሆኑ ተነግሯል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎችም የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀራንዮ አደባባይና ቤተል የችግኝ ተከላ መርሃግብር ላይ ተሳትፈዋል።

በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በቆሼ አካባቢ የችግኝ ተከላ እያከናወኑ ነው።

በአረንጓዴ አሻራ ቀን አገሪቱ 200 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአለምን ክብረወሰን ትሰብራለች ተብሎ ይጠበቃል።

የችግኝ ተከላው መከናወን አገሪቱ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ተሳትፎ የምታሳድግበትና በምስራቅ አፍሪካ አርአያ እንድትሆን የሚያስችላት ነው።

አገሪቱ ለምታካሂደው የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚም አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

በትናንትናው እለት ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ ላይ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት፤ ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ 211 ሚሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል።

በእለቱ የሚተከሉት ችግኞችን የተመለከተ መረጃ በቴክኖሎጂ በተደገፈ ስርዓት የሚሰበሰብ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ካሉት አስተዳደራዊ መዋቅሮች መረጃው የሚሰበሰበውም በየሶስት ሰዓቱ ነው ብለዋል።

መረጃዎቹ የሚሰባሰቡት በቅድሚያ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 3 ሰዓት፣ ቀጥሎም ቀን በ6 ሰዓት እንደዚሁም ከቀትር በኋላ በ9 ሰዓትእና በ12 ሰዓት ይሆናል ብለዋል።

በአጠቃላይ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ የተተከለውን ችግኝ የተመለከተ መረጃ የሚሰበሰብ ሲሆን በአገሪቱ የሚገኙ ዞን አስተዳደሮች በየ20 ደቂቃው የተደራጀ መረጃ ለፌዴራል ማዕከል ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።

የፌዴራል አካላት ደግሞ በየ30 ደቂቃው እንቅስቃሴውን የተመለከተ መረጃ ወደመረጃ ቋት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል።

በተጨማሪም አጭር የፅሁፍ መልእክትን በመጠቀም በቀጥታ መረጃን ማስተላለፍ እንደሚቻልም ተገልጿል።

መረጃው ቀጥታ ወደ ማዕከል ከገባ በኋላ አሰራሩን በሚቆጣጠሩት ባለሙያዎች አማካኝነት ተተንትኖ ለብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ይተላለፋል።

መረጃው ወደ ጽረ-ገጽና ዳታቤዝ የሚለቀቅ መሆኑና ድረ-ገጹ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆኖ የችግኝ ተከለውን ሂደት መከታተል የሚያስችለው ነውም ተብሏል።

ህንድ በዓለምአቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 66 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል በዓለም የክብር መዝገብ ላይ በቀዳሚነት ሰፍራ ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም